በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብአትና ቴክኖሎጂዎችን የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ዶክተር ድረስ ሳህሉ

10 Mons Ago
በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብአትና ቴክኖሎጂዎችን የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ዶክተር ድረስ ሳህሉ

በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብአትና ቴክኖሎጂዎችን የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ገለጹ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ነባሩ እና አዲስ የሥራ ኃላፊዎች የሥራ ርክክብ አካሂደዋል። 

በእዚህ ወቅት የቢሮ አዲሱ ኃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ እንደገለጹት፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የተለያዩ አካላትን የነቃ ተሳትፎና ርብርብ ይጠይቃል።

በክልሉ ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በገጠር እንደሚኖር አስታውሰው፣ የእዚህን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ወቅታዊ ችግር የግብርና ሥራው ላይ ጫና እንዳይፈጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደክልሉ የገባውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ አርሶ አደሩም ከሰላሙ ጎን ለጎን የግብርና ሥራውን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

"በተለይ የግብርና ልማቱን ለማዘመን ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው" ያሉት ዶክተር ድረስ፣ በክልሉ ግብራናውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመረው የመካናይዜሽን አሰራር ይበልጥ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፣ ለግብርና ልማት ሥራ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ገጠር ድረስ ወርዶ ለማሰራጨት አርሶ አደሩ ትብብር ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የቀድሞው የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው እንዳሉት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

"በቅንጅት በተሰራው ስራም በመኸርና በበጋ ስንዴ፣ በአኩሪ አተር ልማት፣ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል" ብለዋል።

በተጨማሪም የሜካናይዜኝን እርሻን ለማስፋፋት የክልሉ መንግስት ከ700 በላይ የእርሻ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉን ተናግረዋል።

አዲሱ የቢሮው አመራርም የክልሉን የሰብል ምርታማናት ለማሳደግ በተለይ ለግብርና ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ዶ/ር ኃይለማርያም አስገንዝበዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top