በሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን የመልማት መብት የማይገድብ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በጥንቃቄ እየተሰራ ነው፡- ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

10 Mons Ago
በሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን የመልማት መብት የማይገድብ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በጥንቃቄ እየተሰራ ነው፡- ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
በህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የኢትዮጵያን የመልማት መብት የማይገድብ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
 
የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተቀመጠለት እቅድ መሰረት ያለምንም እንከን እየተከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በድርድሩ ሂደት ዙሪያ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
በማብራሪያቸውም የሶስትዮሽ ድርድሩ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ማዕቀፎች ስር ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ወስደውት እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ድርድሩ ተመልሶ በአፍሪካ ህብረት ስር እንዲሆን የተሳካ ስራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
 
በዚህም በደቡብ አፍሪካ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብንሊክ ኮንጎ ንግግር ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከታህሳስ 15 ቀን 2022 ጀምሮ መደበኛ ንግግር ተቆርጦ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆኖም ሀገራቱ በአፍሪካ ህብረት በኩል ኢ-መደበኛ ንግግሮችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግብፅ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲጀመር ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መስማማታቸውን ተከትሎ ድርድሩ ዳግም በካይሮ መጀመሩን ገልጸዋል።
 
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ድርድሩ ካቆመበት ርዕሰ ጉዳይ እንዲጀምር በቂ ዝግጅት በማድረግ በድርድሩ መሳተፉን ተናግረዋል።
በካይሮው ድርድር በ16 አንቀፆች ላይ ንግግር በማድረግ በዘጠኙ ላይ የሶስቱንም ሀገራት አዳዲስ ሀሳቦች በመጨመር ድርድሩ በመልካም ሁኔታ መካሄዱን ተናግረዋል።
 
በድርድሩም ሶስቱም አገራት መሳተፋቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች መሆኗን ያነሱት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ፤ ሆኖም በአንዳንድ ተደራዳሪዎች በኩል ስለ አሳሪ ስምምነት እንደሚነሳ ጠቁመዋል፡፡
 
ነገር ግን በድርድር የሚፈረሙ ሰነዶች የኢትዮጵያን የመልማት መብት የማይገድቡና የግድቡ የውሃ አጠቃቀም በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት የማያስከትሉ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ በኩል ድርድሩ ብሔራዊ ጥቅምናና ሉዓላዊ መብትን በሚያስከብር መልኩ እየተመራ ነው ብለዋል፡፡
 
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ አክለውም፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት እቅድ መሰረት ያለምንም እንከን እየተከናወነ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
በዚህም ከዘንድሮው የዝናብ ወቅት በፊት አራተኛውን የውሃ ሙሌት መያዝ የሚያስችለው የግድቡ ከፍታ ግንባታ ዝግጁ መደረጉን ጠቅሰው፤ የውሃ ሙሌቱም በቂ ዝናብ በመኖሩ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በቂ ውሃ እንዲያልፍ በማድረግ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
 
ነገር ግን አንዳንድ አካላት ግድቡን በተለይ ደግሞ የሃይል ማመንጫ ተርባይኖችን በሚመለከት የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን መናገራቸውን ዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
 
መንግስት የተርባይኖች ውጤታማነት አቅም እንዲጨምር በማድረግና አላግባብ የሚባክን ወጪን በመቆጠብ ሃይል የማመንጨቱን ስራ በተቀመጠለት አቅድ እያከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top