የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኦሎምፒክ ቦክሰኛ፡- በቀለ ዓለሙ (ጋንች)

3 Mons Ago
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኦሎምፒክ ቦክሰኛ፡- በቀለ ዓለሙ (ጋንች)

ኢትዮጵያን በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ ስሟ እንዲጠራ ያደረጉ ብዙ እንቁ ስፖርተኞች እና አትሌቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከእነዚህ የሃገር ባለውለታዎች መካከል ደግሞ በቦክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወከለው በቀለ አለሙ (ጋንች) አንዱ ነው፡፡ ከ 59 ዓመታት በፊት በቶክዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው ቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ፤ ኋላም ተከትለው በመጡ የኦሎምፒኮ መድረኮች እና የአፍሪካ ሻምፒዮን  ላይ ሃገሩን ወክሎ መሳተፍ የቻለ ፈር ቀዳጅ ስፖርተኛ ነው፡፡  

ታህሳስ 29 ቀን 1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደው ቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ፤ ገና ከልጅነት እድሜው አንስቶ የቦክስ ፍቅር እንዳደረበት ይነገራል፡፡ በወጣትነት እድሜው የተለያዩ የቦክስ ውድድሮችን እና ትዕይንቶችን እተመለከተ ያደገው በቀለ፤ ስፖርቱን ያለማንም አሰልጣኝና ደጋፊ በግሉ ይለማመድ እንደነበር እና በሂደተም በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ታቅፎ የተለያዩ ከተማ አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ መጀመሩ ይገለጻል፡፡

ቦክሰኛ በቀለ በአዲስ አበባ በሚዘጋጁ የቦክስ ውድድሮች ላይ በሚሳተፍበት ወቅት ብዙ ደጋፊዎች እንደነበሩት የሚነገር ሲሆን፤ በየሳምንቱ በየሲኒማ ቤቱ በቦክስ አፍቃሪዎች ታጅበው ውድድሮች ሲካሄዱ የበቀለን (ጋንች) ሃይለኛ ግራ ቡጢ ለመመልከት ሲኒማ ቤቶች ይጨናነቁ ነበር፡፡

በጊዜው የነበሩት እንደ ሲኒማ ራስ፣ ሲኒማ አዲስ ከተማ፣ ሲናማ አድዋ ያሉ የቦክስ ውድድር መካሄጃዎች፤ በቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ ብቃት ይበልጡኑ እየደመቁ እና ብዙ ተመልካች እያገኙ መምጣታቸው ይነገራል፡፡

ቦክሰኛ በቀለ በተለይም በወቅቱ በቦክሱ ስማቸው ጎልቶ ይጠራ ከነበሩት ቦክሰኛ ማሞ በየነ፣ ቦክሰኛ አሰፋ ጎሬላ እና ቦክሰኛ ጉዲሳ ሆራ ጋር የሚያደርጋቸው የተለያዩ የቦክስ ውድድሮች ስሙን ይበልጥ ታዋቂ ያደረገው ሲሆን፤ በቦክስ አፍቃሪው ማህበረሰብ የወጣለት "ጋንች" የሚለው ስያሜም ከአዲስ አበባ ከተማ አልፎ በኢትዮጵያ ደረጃ እየታወቀ መጣ፡፡

ቦክሰኛ በቀለ በግሉ በተለያዩ የቦክስ ውድድሮች ላይ በሚሳተፍበት ወቅት፤ በዘርፉ ብዙ ክለቦች እንዳልነበሩና እና የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን እንኳን አለመመስረቱ ይነገራል፡፡

በዚህ ወቅት አቶ በቀለ በተለያዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ብሎም፤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ እንዲያስችለው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አመልክቶ የነበረ ሲሆን፤  በዚህም መሰረት ከክለቡ ባገኘው ፈቃድ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ውድድሮችን በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስም ማድረግ ጀመረ፡፡

ቦክሰኛ በቀለ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስም የተለያዩ ውድድሮችን እያደረገ ከመጣ በኋላ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቦክሱ ዘፍር ኢትዮጵያን በመወከል በኦሎምፒክ መድረክ ለመሳተፍ የሚስችለውን እድል አገኘ፡፡ ጋንች በቦክሱ ዘርፍ በሮም ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመሳተፍ ወደ ጣልያን ዋና ከተማ ሮም ለማምራት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት በበጅት እጥረት ምክንያት የቦክሰ ቡድኑ መቀነሱን ተከትሎ በውድድሩ ላይ የመካፈል እድሉን ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ጋንች በሮም ኦሎምፒክ ያጣውን የመሳተፍ እድል በ1957 በተካሄደው የቶክዮ አሎምፒክ መልሶ ያገኘ ሲሆን፤ በዚህም በተሻለ ስልጠና እና ዝግጅት በኦሎምፒክ ወድድድሩ ስኬታማ ሊባል የሚችል ተሳትፎን ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህ ትልቅ የአለም አቀፍ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ስም መወከል የቻለው ጋንች፤ በቦክሱ ዘርፍ ሃገሩን ወክሎ በመሳተፍ ፈር ቀዳጅ እና ለብዙ ስፖርተኞችም አርአያ መሆን ችሏል፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1968 በሜክሲኮ በተደረገው ኦሎምፒክ ላይ ዳግመኛ ሃገሩ ኢትዮጵያን በቦክስ የወከለው ጋንች፤ በዚህኛው መድረክም በተሻለ ስራ እና በጠንክራ ዝግጅት በዘርፉ የላቀ ልምድ ካላቸው የሌሎች ሀገራት ቦክሰኞች ጋር በመፎካከር የተሳትፎ ሜዳሊያን አግኝቷል፡፡

በሁለት ትልልቅ የኦሎምፒክ መድረኮች ላይ አሰልጣኛና የተሟላ ትጥቅ ሳይኖረው ሃገሩን ወክሎ መሳተፍ የቻለው ጋንች፤ በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው የአፍሪካ የቦክስ ሻምፒዮን ላይ አሸናፊ በመሆን ሃገሩን በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ማስጠራት የቻለ ስፖርተኛ ነው። ቦክሰኛ በቀለ አለሙ በ2004 ዓ.ም የህይወት ታሪኩን የሚዳሰስ "ያልተነገረለት የአገር ባለውለታ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀም መጽሐፍ ታትሞለተል።

የ11 ልጆች አባት የነበረው ቦክሰኛ በቀለ አለሙ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ82 ዓመቱ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት በአዲስ አበባ ሸጎሌ በሚገኘው  ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን የቀብር ስነ-ስርዓቱ ተፈፅሟል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top