በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ወደ 80 የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰልፈው የነበረ ሲሆን በወቅቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "መሰረታዊ መስፈርቶችን የማያሟሉ” በማለት 26 ያህሉን የሰረዘ ሲሆን ከ50 በላይ ህጋዊ ፓርቲዎች ለምርጫ ብቁ መሆናቸውን በወቅቱ መግለፁ ይታወሳል።
ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ከምርጫ በኋላ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው ለምን ጠፋ ሲል ጠይቋል።
በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ ፍቃዱ ሀንድኖ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር በምርጫ ሰሞን ብቻ የሚግል መሆን የለበትም ብለዋል።
በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢገኙ የወከሉትን ህዝብ ድምጽ ማሰማትና ዓላማቸውን ማሳተዋወቅ አለባቸው ያሉ ሲሆን ይህ ካልሆነ በምርጫ ወቅት ከህዝባቸው ፊት የመቆም ጥንካሬ ከወዴት ያገኛሉ ሲሉ ይጠይቃሉ።
በምርጫ ወቅት የነበሩት በርካታ ፓርቲዎች አሁን ስራቸውን የጨረሱ መስለው ጠፍተዋል የሚለው የእናት ፓርቲ፤ እነዚህን ፓርቲዎች ለወከላቸው ህዝብ እንኳን የማይታመኑ በፓርቲ ስም ፖለቲካውን የሚያቀጭጩ ናቸው ብሏል።
ለዜጎች ችግር መፍትሔ ለመጠቆም ሁልጊዜም ክትትል እናደርጋለን የሚለው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፤ እንደ ፓርቲ በየትኛውም ሀገራዊ አጀንዳ ላይ ተሳትፎ ብናደርግም ገዥው ፓርቲ ከስብሰባ ያለፈ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሀሳብ አያካትትም ነው ያለው፤ አሳታፊነቱ በተግባር እንዲረጋገጥም ጠይቋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በበኩሉ፣ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ቢኖረንም እንደሀገር ያሉ የሰላምና ደህንነት ችግሮች ህዝባችንን እንዳናገኝ አድርገውናል ብሏል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገዥው እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የጋራ ምክር ቤት ማቋቋማቸው በበጎ የሚነሳ ነው የሚለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመፍትሔ አካል ለመሆን እየሰሩ ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ በምርጫ ወቅት የሚታየው የፓርቲዎች እንቅስቃሴ በሌሎች ጊዜያትም እንዲኖር ምቹ የፖለቲካ ምህዳርን መፍጠር ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ምክርቤቱ አሳስቧል።
በአስረሳው ወገሼ