በኢትዮጵያ በ10 ዓመታት ውስጥ አምስት የፈጣን መንገዶች ግንባታ ለማከናወን እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

11 Mons Ago
በኢትዮጵያ በ10 ዓመታት ውስጥ አምስት የፈጣን መንገዶች ግንባታ ለማከናወን እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

በኢትዮጵያ በ10 ዓመታት ውስጥ በተለያዩ አከባቢዎች 1 ሺህ 349 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ አምስት የፈጣን መንገዶች ግንባታ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።

የአስተዳደሩ የፈጣን መንገድና ልዩ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ትግበራ ቡድን መሪ ኢንጂነር ችሮታው ይርጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በ10 ዓመት ውስጥ በአገሪቱ በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች የፈጣን መንገድ ግንባታ ለማካሄድ ታቅዷል።

የፈጣን መንገዶቹ የሚገነቡት ከአዲስ አበባ - ደሴ፣ ከአዲስ አበባ - ጅማ፣ ከአዲስ አበባ - ደብረ ማርቆስ፣ ከአዋሽ- ሜኤሶና ከአዲስ አበባ -ነቀምት መሆኑን ጠቅሰው አጠቃላይ የመንገዶቹ ርዝመት 1 ሺህ 349 ኪሎ ሜትር መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ 658 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታው በመንግሥት እና የግል አጋርነት ማዕቀፍና በልማት አጋሮች የፋይናንስ ድጋፍ በ64 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ በቅድሚያ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንገዶቹም ከአዲስ አበባ - ወልቂጤ፤ ከአዲስ አበባ - አምቦ፤ ከአዲስ አበባ - ደብረ ብርሃን፤ ከአዋሽ ሜኤሶ እና ከአዲስ አበባ ጎሐጽዮን መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የዓለም ባንክ ከአዋሽ ሜኤሶ ለሚገነባው የ142 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ብድር መፍቀዱን አንስተዋል።

ከቀናት በፊት የገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክ ለአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት (በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ፕሮጀክት) የ730 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ሥምምነት ተፈራርመዋል።

በሥምምነቱ የፋይናንስ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ከአዋሽ-ሜኤሶ የሚገነባው የ142 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ አንዱ ነው።

የገንዘብ ድጋፉ በዚሁ መንገድ አቅራቢያ የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የጤና፣ ትምህርትና መጠጥ ውሃ ተደራሽነታቸውን ለማሻሻልና ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኟቸውን መንገዶች ለመገንባት ጭምር ይውላል።

የፍጥነት መንገዱ በጋላፊ በኩል ወደ ጂቡቲ የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚቀንሰው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከባቱ - አርሲ ነገሌ እስከ ሃዋሳ የሚደርሰውና በሁለት የሥራ ተቋራጮች የሚገነባው የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቶች በመፋጠን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም 57 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የባቱ - አርሲ የፍጥነት መንገድ ግንባታ አሁን ላይ አፈጻጸሙ 63 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።

ግንባታው ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እየተካሄደ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የአርሲ ነገሌ - ሃዋሳ የ52 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታም አፈጻጸሙ 58 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ፣ ሌላው የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ቀጣይ ክፍል የሆነውና ከአዳማ አስከ አዋሽ የሚገነባው 60 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ጂ ኤም ሲ በሚባል የሕንድ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ በ6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

የፈጣን መንገድ ፕሮጀክቶቹ ቀጣናዊ ትስስርን የማሳደግ ፋይዳ እንዳላቸውም የገለጹት የቡድን መሪው የአገሪቱን የወጪ ገቢ የንግድ እንቅስቃሴ በትራንፖርቱ ዘርፍ ለማሳለጥም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top