በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያን ታሪክ የቀየሩ ድሎች የተመዘገቡበት ስኬታማ ዓመት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ፤ በ2015 ዓ.ም የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ወደ ውጭ መላክ የተጀመረው በዚሁ ዓመት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የኢትዮጵያን ስምና ታሪክ የቀየረ ዐቢይ ድል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ጥሎ የነበረው የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ ውይይት እልባት እንዲያገኝ መደረጉ ኢትዮጵያዊያን ያለማንም ጣልቃገብነት ችግራቸውን መፍታት እንደሚቻል ያሳዩበት መሆኑን አንሥተዋል።
በዲፕሎማሲው መስክም በዓለም አቀፍ እና በቀጣናው ላይ ወሳኝ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ያስቻሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የ2015 ዓ.ም ብሔራዊ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ እንደሚወሰድ ጠቅሰው፣ ይህም የኢትዮጵያን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል የተገባደደበት እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ዕውቅና እንድታገኝ ያስቻለ የልማት ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓመቱ አገርን ወደተሻለ ምዕረፍ ማሸጋገር ያስቻሉ ድሎች ቢመዘገቡም ፈታኝ ጉዳዮች አጋጥመው እንደነበር አስታውሰዋል።
ዜጎችን እየፈተነ የሚገኘው የኑሮ ውድነት እና የሰላም እጦትም በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የ2015 ዓ.ም ከተከሰቱ ተግዳሮቶች ተጠቃሽ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመሆኑም በአዲሱ የ2016 ዓ.ም መንግሥት ዜጎችን እየፈተነ ለሚገኘው የኑሮ ውድነት እና የሰላም እጦት ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።