18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አስተባባሪ አቢይ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ የ18ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መነሻ እቅድ ላይ ተወያይቷል፡፡
በዓሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ ‘ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት’ በሚል መሪ ሀሳብ በድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል።
ውይይቱን የመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዓሉ የሕዝቦችን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ትስስር በማጠናከርና በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመትና በቀጣይ በሚከበሩት በዓላትም እነዚህ ነጥቦች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩ ጠቁመው በአገራችን የሕግ የበላይነት እስኪከበርና ሕገ መንግሥታዊነት ባህላችን እስኪሆን ድረስ በትጋትና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሠረት የሚሆኑ ውይይቶችና ምክክሮች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል።
በሲዳማ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት የተካሄደው 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔሮችና ሕዝቦች ቀን በዓል በተሳካ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉንና ለዚህም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱት ለክልሉ ሕዝብና አመራሮች ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘንድሮ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሱማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት በድምቀት እንደሚከበር ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።