በአዲስ አበባ ከተማ ምሽትን ጠብቆ እስከ እጥፍ ጭማሪ የሚደረግበት የታክሲ ታሪፍ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
“ከሥራ መውጫ ባለው ሰዓት ላይ በተለይ ደግሞ መምሸቱን ተገን ተደርጎ ጭማሪ እየተደረገብን ይገኛል፤ ሆኖም ግን መሔድ የምንፈልግበት ቦታ መድረስን ታሳቢ በማድረግ የመጠየቅ ሁኔታ የለም፤ ከስንት አንዴ ስንጠይቅም ‘ካልተስማማችሁ ውረዱ’ የሚባል ምላሽ ይሰጠናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ አጋርዋል።
ይህንን ሐሳብ በመንተራስ ስለ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳይሬክተር የሆኑትን ወ/ሮ እፀገነት አበበን አናግረናል።
ኃላፊዋ በሰጡት ምላሽ “በመዲናዋ ያለውን የኪሎ ሜትር ርቀት መሠረት በማድረግ ታሪፍ አውጥተናል፤ ሆኖም ግን የሰዓቱን መምሸት ተገን አድረገው ታሪፍን በእጥፍ ወይም ከታሪፍ በላይ ከሚጨምሩ የታክሲ አሽከርካሪዎች ማኅበረሰቡን ለመጠበቅ ሕጋዊ የዋጋ ተመኑን ተጠቃሚዎች ያውቁት ዘንድ አሽከርካሪዎች ጽፈው እንዲለጥፉ እና ተሳፋሪዎችም በሱ መሠረት እንዲከፍሉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በመሥራታችን አሁን ላይ አብዛኛው ማኅረሰብ ታሪፉን እንዲያቅ አድርገናል” ብለዋል።
በተጨማሪም ድንገተኛ ፍተሻዎችን በማድረግ እና በ11ዱም የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያሉ የስምሪት እና ቁጥጥር ሠራተኞች ከጠዋቱ 12:45 እስከ ምሽት 2:00 ሰዓት ድረስ የቁጥጥር ሥራዎችን እንዲሠሩ በማድረጋችን በ2015 ዓ.ም ወደ 62 ሺህ 319 የሚጠጉ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ እና እየቆራረጡ የሚጭኑ፣ የሕግ ተላላፊ የሆኑ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
ምንም እንኳን ዳይሬክተሯ ያሉት አሠራር ቢኖርም መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ እንዳልሆነ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
የቅሬታ መስጫ የተባሉት የስልክ መስመሮች አለመነሣታቸው እና በታክሲ ውስጥ ሆነው ቢቃወሙ እና ነገሮች ወደ ግርግር ቢቀየሩ ከማን ፍትሕ እንደሚያገኙ አለማወቃቸው ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ሆኖም እነዚህን አካላት ለማስቆም በአጭር የስልክ መስመር 9417 ላይ አንዲሁም በአቅራቢያ ለሚገኝ የትራፊክ ፖሊስ እና የመሥሪያ ቤቱ ስምሪት መጠቆም የሚቻል ሲሆን ይህንን ድርጊት መግታት የመንግሥት ሚና ብቻ ስላልሆነ ማኅበረሰቡ መረባረብ እና አንድ ሆኖ በተቃውሞ መቆም አለበት ብለዋል። ይህ ደሞ ማኅበራዊ መረዳዳት ብቻ ሳይሆን በመተባበር ሥር የሚፈረጅ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታም ጭምር መሆኑን አንሥተዋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ሕዝብ እንደዚህ ያሉ ያልተገቡ ድረጊቶች ሲፈፀሙበት ከዝምታ እና ከመተው ይልቅ መብቱን ማስከበር አለበት ብለዋል።
ኅብረተሰቡ የድርጊቱ ተባባሪ ባለመሆን ነገሮች ወዳልተገባ ሲሄዱም ለትራፊክ ፖሊሶች ብቻ ሳይሆንም ለፍትሕ አስፈፃሚ አካላት በማሳወቅ መብቱን ማስከበርን መልመድ እንዳለበት ነው ያነሡት።
በተጨማሪም ይህ ጉዳይ በቀጥታ ሚመለከተው መሥሪያ ቤት ለማኅበረሰቡ በትክክል የሚሠሩ የስልክ መስመሮችን በመዘርጋት እና ለሚደርሰው ጥቆማ እና ምልከታ ከገንዘብ የዘለቀ እርምጃን መውሰድ ችግሩን ካለበት በበለጠ እንዳይስፋፋ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን እንደ ዋንኛ ምክንያት የሚቀመጠውን የተደጋጋመ የታሪፍ ክለሳ፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ሁነኛ መፍትሔ በማበጀት ከምንጩ ለማድረቅ መሞከር ሁነኛ መንገድ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
በአፎሚያ ክበበው