የፕሪጎዢን ሞት አደጋ ወይስ....?

3 Mons Ago
የፕሪጎዢን ሞት አደጋ ወይስ....?

ከ1 ዓመት ከ6 ወር በላይ በኔቶ እና ምዕራባውያን ስልታዊ ከበባ እየተደረገብኝ ነው በማለት ከዩክሬን ጋር በውክልና ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሩሲያ በዚህ ጦርነት ምክንያት በርካታ ጂኦፖለቲካል ለውጦችን እያስመለከተችን ትገኛለች።

ታዲያ በዚህ ጦርነት ከሩሲያ የጦር ኃይል በተጨማሪ ዋግነር ተብሎ የሚጠራውና ቅጥረኛ ወታደራዊ ተዋጊ እንደሆነ የሚነገርለት የሩሲያ ቡድን አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም። በ2014 ሩሲያ ክሬሚያን ከዩክሬን እጅ ፈልቅቃ በእጇ ስታስገባ የዚህ ወታደራዊ ቅጥረኛ ቡድን ስም እና ጀብዶች በዓለም ዙሪያ ተሰሙ።

ዋግነር ለፑቲን ቀኝ እጅ እንደሆነ ይነገርለት በነበረው ዬቭጊኒ ፕሪጎዢን ይመራ ነበር። ነገር ግን ከወራት በፊት ዋግነር “ጥቃት አድርሶብኛል” በሚል ከሩሲያ ጦር ጋር ተቃቃረ አፈሙዝ ተማዘዘ፣ ፕሪጎዢንም ፑቲንን በነገር ይሸነቁጡ፤ ቁጣቸውን ያዘንቡ ያዙ።ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ዋግነር ከሀገሪቱ ጦር ጋር የገባው እሰጣ ገባ መፈታቱ ፑቲንም ከቀድሞ አጋራቸው መምከራቸው ተነገረ። ይህ በሆነ በ1 ወር ልዩነት ግን ዬቭጊኒ ፕሪጎዢን በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸው ተሰማ።

የዛሬው የሳይበር ዓለም አቀፍ ትንታኔ በሌኒንግራድ ተወላጁ ዬቭጊኒ ፕሪጎዢን የህይወት ታሪክና የአሟሟቱ ውዝግብ ላይ ያተኩራል።

በጎርጎሮሲያኑ የዘመን ቀመር በሰኔ 1 ቀን 1961 ዓ.ም በቀድሞዋ ሌኒንግራድ- ሶቪየት ዩኒየን በአሁኗ ሴንት ፒተርስበርግ-ሩሲያ ተወለደ፤ ዬቭጊኒ ፕሪጎዢን።

እናቱ ቫዮሌታ ኪሮቭና የሆስፒታል ነርስ ነበረች፤ አባቱ ቪክቶር ዬቭጄኒቪች የማዕድን መሐንዲስ የነበረ ሲሆን ዬቭጊኒ ፕሪጎዢን ገና የ9 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ህይወቱ ያለፈው።

የፕሪጎዢን አጎት የፊም ኢሊች የቀድሞዋ ሶቪየት ሳይንቲስት  ነበር።ታዲያ ፕሪጎዢን በልጅነቱ ከየፊም ጋር በዩክሬን ዞሆቲ ቮዲ ለብዙ ዓመታት ኖሯል።

የፕሪጎዢን እንጀራ አባት ሳሙኤል ፍሪድማኖቪች የበረዶ መንሸራተት ስፖርት አስተማሪ ነበር፣  ፕሪጎዢንም በዚህ ምክንያት ከበረዶ መንሸራተት ስፖርት ጋር ተዋወቀ። ፕሮፌሽናል የበረዶ ሸርተቴ ተወዳዳሪ ለመሆንም ለመሆን በመፈለግ በ 1977 ከሌኒንግራድ ስፖርት አዳሪ ትምህርት ቤት ተመረቀ። ነገር ግን በጉዳት ምክንያት ከዚህ ስፖርት ርቋል፣ በኋላም በልጆች የስፖርት ትምህርት ቤት የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሆኖ ሰርቷል።

አመጸኛው ፕሪጎዢን

እ.አ.አ. በ1979 የ18 ዓመቱ ፕሪጎዢን የመጀመሪያውን ወንጀል ስራ ሲሰርቅ ተይዞ የሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስራት ተቀጣ።

እ.አ.አ. በ1980 ፕሪጎዢን ከእስር ተፈቶ ወደ ሌኒንግራድ ተመለሶ ከአካባቢው የቀማኞች ቡድን ጋር ተቀላቀለ። ከዚያም በድጋሚ በሌኒንግራድ አካባቢ በተፈፀመ የስርቆት ዘመቻ ላይ ተሳትፏል። በድጋሚ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመንገድ ላይ አንዲት ሴትን ሲዘርፉ ተይዞ 12 ዓመት ተፈርዶበት በድጋሚ ዘብጥያ ወርዷል።

ነገር ግን ፕሪጎዢን በማረሚያ ቤት ቆይታው ራሱን በብዙ ነገሮች ለወጠ። መጽሀፍትን ማንበብ ጀመረ እንዲሁም በሙያ ትምህርት ቤት ስልጠና ወስዶ እንደ ኦፕሬተርነት፣ ሹፍር እና የእንጨት ስራ የመሳሰሉ ሙያዎችን ቀስሟል። በ1988 የሶቪየት ዩኒየን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሪጎዢን ጸባዩ ላይ ለውጥ ማሳየት መጀመሩን ተከትሎ ቅጣቱን ወደ አስር ዓመታት ዝቅ አደረገለት።

ፕሪጎዢን እስረኞች የዋግነር ቡድንን እንዲቀላቀሉ ለማሳመን እሱ በእስር ቤት ያሳለፈውን ጊዜ በመንገር ይጠቀምበት እንደነበር እና በዚህም ውጤታማ ሆኖ ብዙዎችን እንዳሳመነ የዋግነር ቡድን ጓዶቹ ይገልጻሉ።

ፕሪጎዢን ከእስር በኋላ

ፕሪጎዢን ከእስር ከተፈታ በኋላ በሊኔንግራድ ጎዳናዎች ከእናቱ እና ከእንጀራ አባቱ ጋር ፈጣን ምግቦችን በማብሰል መሸጥ ጀመረ። ፕሪጎዢን በአንድ ወቅት ከኒዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ስለዚህ ጊዜ እና ስለ ስራው ሲናገር የፈጣን ምግቦቹ ስራ አዋጭ እንደነበር እና በርካታ ገንዘብ እንደሰሩበትም ገልጿል።

ከሶቪየት ኅብረት ውድቀት በኋላ ፕሪጎዢን የዘመኑን ሥራ ፈጣሪነት መንፈስ በመከተል በብዙ አዳዲስ ንግዶች ውስጥ መስራች እና ተሳተፊ ሆነ።

እ.ኤ.አ በ1995 የሌሎች ንግዶቹ ገቢ ማሽቆልቆል ሲጀምር ፕሪጎዢን ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ወደ ሬስቶራንት ንግድ ገባ። 

በሬስቶራንቱ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ደካማ የስራ አፈጻጸም ወይም የስነምግባር ጉድለት ካሳዩ ፕሪጎዢን ከባድ ቅጣት ይቀጣ እንደነበርም ይነገራል።

የፕሪጎዢን እና የፑቲን ትውውቅ ጥንስስ

ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ ፕሪጎዢን እና ፑቲን የተወለዱት በቀድሞዋ ሌኒንግራድ በአሁኗ ሴንት ፒተርስበርግ ነው። እ.አ.አ. በ2000 ዎቹ መጀመሪያ ነበር ፤ ፕሪጎዢን በወዳጅነት ለበርካታ ዓመታት አብረው ከዘለቁት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የተቀራረቡት።

ከዚህ በኋላ ኮንኮርድ የተሰኘው የፕሪጎዢን ምግብ አቅራቢ ድርጅት የፑቲንን በዓለ - ሲመት ስነስርዓት፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በሴንት ፒተርስበርግ ያደረጉትን ጉብኝት ጨምሮ ለመንግስት ባለስልጣናት የተሰናዱ የእራት ግብዣ ልዩ እና አትራፊ የመንግስት መሰናዶዎችን አስተናግዷል። እነዚህ ስራዎች ፕሪጎዢንን "የፑቲን ሼፍ" የሚል ቅጽል ስም እንዲያገኝ አድርገውታል።

ታዲያ ስራው ይህን ሰው ፈርጠም ያለ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖረውም አድርጓል። ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2012 የቅርጫት ኳስ ሜዳ እና የሄሊኮፕተር ማረፊያ ያለው የተንጣለለ ቪላ በሴንት ፒተርስበርግ ገንብቷል።

ከዚህ ባለፈም ፕሪጎዢን በዚህ ጊዜ የግል ጄት እንዲሁም ቅንጡ ጀልባ ነበረው። ፕሪጎዢን በርካታ አውሮፕላኖች እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል ሁለት ሴስና 182s፣ ኢምብሬር ሌጋሲ 600፣ ብሪቲሽ ኤሮስፔስ 125 እና ሀውከር 800XP የተሰኙ የአውሮፕላን አይነቶች ይጠቀሳሉ። ሆኖም ፕሪጎዢን እንቅስቃሴውን በምግብ ኢንዱስትሪው ላይ ብቻ አልገደበውም።

ፕሪጎዢን እና ዋግነር

የዋግነር ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው እ.ኤ.አ. በ2014 ፣ ሩሲያ ክሬሚያን ወደ ግዛቷ በቀላቀለችበት ወቅት ነው። እስከ 2022 ድረስም ይሁን ቡድን ማን ይመስርተው ማን ይምራው የሚታወቅ ነገር አልነበረም። የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት በታወጀበት ወቅት ግን ፕሪጎዢን ዋግነርን እንደመሰረተ እና  የቡድኑ መሪ እንደሆነ በይፋ ታወቀ።

እ.ኤ.አ. በ2016 መጀመሪያ ላይ ዋግነር 1ሺህ ወታደሮች ነበሩት ፣ በኋላም በነሐሴ 2017 ወደ 5ሺህ እንዲሁም በታህሳስ 2017 ወደ 6ሺህ ከፍ ብሏል ። ድርጅቱ በአርጀንቲና የተመዘገበ ሲሆን በሴንት ፒተርስበርግ እና ሆንግ ኮንግ ቢሮዎች አሉት ።

በአሁኑ ወቅት 25 ሺህ ወታደሮችም እንዳሉት ይገመታል፤ የዋግነር ቡድን በእጁ ላይ ከባድ የጦር መሳሪያዎች አሉት። ለምሳሌ የአየር መቃወሚያ መሳሪያዎች እና SA-22 የውጊያ ተሽከርካሪዎች ይጠቀሳሉ።

ቡድኑ ክሪሚያን ነጻ ከማውጣት ዶንባስን ለሩሲያ ከማስመለሱ በተጨማሪ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎችን ማለትም በምስራቅ አውሮፓ - ዩክሬን እና ቤላሩስ፣ በመካከለኛው ምስራቅ በሶሪያ፣ በአፍሪካ - በሴንትራል አፍሪካ፣ በማሊ እና ሊቢያ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ ቬንዝዌላ ይህ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መኖሩ ይገለጻል።

ይህ ቡድን የሩሲያን መንግስት ጥቅም ለማስከበር በተለያዩ አካባቢዎች በፑቲን ቀኝ እጅ በነበሩት ፕሪጎዢን እየተመራ ዘምቷል። በርካታ ድሎችንም አስመዝግቧል ነገር ግን ሳይጠበቅ አንድ ነገር ተከሰተ፤ የፑቲን ቀኝ እጅ የፑቲን ሼፍ እና ታማኝ ሰው የተባሉት ፕሪጎዢን እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው በተንቀሳቃሽ ምስል ብቅ አሉ።

በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ፕሪጎዢን የሩሲያ ጦር በዩክሬን የሚገኙ የዋግነር ካምፖችን ማጥቃቱን እና በርካታ የተዋጊ ቡድኑ አባላትን መግደላቸውን ሲገልጹ ይስተዋላል።

የፕሪጎዢን የዋግነር ተዋጊዎች በዕለቱ የውጊያ አቅጣጫቸውን ቀይረው አፈሙዛቸውን ወደ ሩሲያ አዞሩ። በዛው ዕለትም በዩክሬን ያለውን ጦርነት በዋናነት የሚቆጣጠረውን እና በሮስቶቭ ኦን-ዶን የሚገኘውን የሩሲያ ወታደራዊ መምሪያ ተቆጣጠሩ። ይህ ነው እንግዲህ በፑቲን እና በታማኝ ቀኝ እጃቸው መሐል ይፈጠራል ተብሎ ያልተገመተውን መቃቃር እንዲፈጠር ያደረገው።

የዋግነርን አፈሙዝ ማዞር ተከትሎም ከጀርባችን ተወግተናል ያሉት ፑቲን ክቡር ዘበኛቸውን ጨምሮ የሀገሪቱን ጦር በተጠንቀቅ ማቆማቸውን ተከትሎ በሩሲያ ከባድ ደም መፋሰስ ይፈጠራል የሚል ስጋትም ሰፍኖ ነበር።ይህን ክህደት የፈጸሙት ሁሉ የእጃቸውን ያገኛሉም ብለው ነበር ፑቲን በሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው።

ነገር ግን ይህ ውጥረት ብዙም ሳይቆይ ረግቦ ዋግነርም በያለበት ትጥቁን እንዲፈታ እና ከሩሲያ ጦር ጋር እንዲቀላቀል ተደረገ። ቤላሩስም ሁለቱን ወገኖች ብቻዋን ለማሸማገል ላይ ታች እያለች ፕሪጎዢንም አንዴ ቤላሩስ አንዴ ሴንት ፒተርስበርግ ናቸው እየተባለ ቀናቶች አለፉ። ከቀናት በኋላ ቭላድሚር ፑቲን በክሬምሊን የቀድሞ ቀኝ እጃቸውን ጨምሮ ከ30 በላይ የዋግነር አዛዦች ጋር ለሶስት ሰዓታት መከሩ፣ ነገሩም በዚህ የለዘበ መሰለ።

ታዲያ የዋግነሩ መሪ ፕሪጎዢን ድምጻቸውን አጥፍተው ከርመው ባለፈው የፈረንጆቹ ነሐሴ 22 ከወደ አፍሪካ በተቀረጸ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች አንድ መረጃን አጋሩ። በንግግራቸውም “በዚህ ባለሁበት ቦታ ሙቀቱ ከ50 ዲግሪ በላይ ነው፤ ዋግነር ሩሲያን በአፍሪካ ብሎም በመላው ዓለም ተጽዕኖዋን እያሳደገ ይገኛል፤ አፍሪካውያን ፍትህ እንዲያገኙና ደስተኛ እንዲሆኑ እየታገልን ነው” ሲሉ ይደመጣሉ።

ከዚህ በኋላ በአውደ ውጊያ ሲሰማራ ግርማ ሞገሱ ያስፈራል የሚባለው ኤቪግኒ ፕሪጎዢንን ጨምሮ 10 የዋግነር አመራሮች ባለፈው ሳምንት በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ።

ከብዙ ውዝግብ በኋላ በዲኤንኤ ነበር ኤቭጊኒ ፕሪጎዢን በተከሰከሰው አውሮፕላን ላይ ህይወታቸው ካለፉት መካከል መሆናቸው የተረጋገጠው።

ምን አልባትም በሁለቱ መካከል ተፈጥሮ በነበረው ቁርሾ መነሻ ከፕሪጎዢን ሞት ጀርባ እጃቸው ሊኖር ይችላል ተብሎ በተለያዩ ሚዲያዎች ስማቸው ሲነሳ የነበሩት ፑቲን፥ የፕሪጎዢንን ሞት አስመልክቶ ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ ላይ ፕሪጎዢን ምንም እንኳን አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም ለዓላማው ቆራጥና ጀግና ነበር፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን እመኛለሁ ብለዋል።

የተዋጊ ቡድኑ ዋግነር መሪ የነበረው ኤቭጌኒ ፕሪጎዢን ሥርዓተ ቀብርም በሴንት ፒተርስበርግ ተፈጽሟል። የፕሪጎዢን የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በትውልድ ከተማው ጥቂት ሰዎች በተገኙበት መሆኑ ተገልጿል።

በስርዓተ ቀብሩ ላይ ፑቲንን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትም አልተገኙም ነው የተባለው። በርካቶች አስተያየቶቻቸውን በኤቭጊኒ ፕሪጎዢን ህልፈተ ህይወት ላይ እየሰጡ ይገኛሉ።

በሰለሞን ከበደ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top