የትኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የህዝቡን የሞራል እሴቶች ማክበር ተቀዳሚ ግዴታው ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን

1 ዓመት በፊት 1006
የትኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የህዝቡን የሞራል እሴቶች ማክበር ተቀዳሚ ግዴታው ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን

የትኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም እና የህዝቡን የሞራል እሴቶች ማክበር ተቀዳሚ ግዴታው መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ኤፍ ኤም አዲስ 97̏.1 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በእርዳታ ስም ከማህበረሰቡ ባህል እና ሞራል ያፈነገጡ ተግባራት ላይ እንዳይሰማሩ ምን እየሰራችሁ ነው? የሚል ጥያቄ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አንስቶ ነበር።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች ሲሰሩ "የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች እና የህዝቡን የሞራል እሴቶች ማክበር ለድርድር የማይቀርቡ ግዴታዎች ናቸው" ያሉት አቶ ፋሲካው ይህን ለማረጋገጥ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ክትትል እና ግምገማ በየግዜው እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላለፉት አስር ዓመታት የነበረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሻሻሉን ተከትሎ ባለፉት አራት ዓመታት ከ4700 በላይ ድርጅቶች ቀርበው መመዝገባቸውን የገለፁት ም/ዋና ዳይሬክተሩ "አገራዊ ጥቅማችንን የሚጎዳ እና  የህዝባችንን የኖረ መልካም እሴት የሚጻረር ነውር ተግባር ላይ የተሰማራ ድርጅት ካለ መቼም አንታገሰውም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሰሞኑን ከህዝብ ሞራል እና ከማህበረሰብ እሴት የተቃረነ ዓላማ ያላቸው አካላት ከባለስልጣን መስሪያ ቤታችን የተሰጠ ፍቃድ አስመስለው በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚያዘዋውሯቸው ሰርተፍኬቶች የሃሰት/fake/ መሆናቸው ይታወቅልኝ የሚል መግለጫ የሲቪክ  ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አውጥቷል።

በአስረሳው ወገሼ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top