በካናዳ ኦንቶሪዮ ከንብ ቀፎዎች ያመለጡ 5 ሚሊዮን ንቦችን ለመቆጣጠር ፖሊስ ንብ አናቢዎችን እርዳታ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡
ቀፎዎቹ የክረምቱን ቅዝቃዜ ተከትሎ ለንቦቹ የቦታ ለውጥ ለማድረግ በመኪና ሲጓጓዙ እንደነበረም ተመላክቷል፡፡
የቀፎዎቹ ማሰሪያ ተፈቶ የመኪና መንገድ ላይ ከወደቁ ቀፎዎች ያፈተለከው 5 ሚሊዮን የንብ መንጋ 400 ሜትር የሚያህል ቦታ ሸፍኖ እንደነበረ ተነግሯል፡፡
ከፖሊስ ተደውሎ እርዳታ ከተጠየቁ ንብ አናቢዎች መካከል አንዱ የሆነው ማይክል ባርበር “ቦታው ላይ ስደርስ ሰማዩ በንብ መንጋ ተጋርዶ ነበር” ይላል፡፡

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በፍጥነት ወደ መኪናዎች እንዲገቡ እና መስኮታቸውን እንዲዘጉ በማድረግ የአደጋውን መጠን በእጅጉ መቀነስ መቻሉንም አስታውቋል፡፡
ቀፎዎቹን ሲያጓጉዝ የነበረው የመኪና ሹፌር ከ100 ጊዜ በላይ ተነድፏል የሚለው ንብ አናቢው በሌሎች ጥቂት ሰዎች ላይም መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ገልጿል፡፡
የንብ መንጋው በፖሊሶች እና ንብ አናቢዎች ትብብር ወደ ቀፎዎቹ እንዲመለስ መደረጉን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡