የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ “ሩቅ ምስራቅ ሳለሁ” ሲል ያዜመላት “የተወዳጇ ጃፓናዊት” መዲና ቶኪዮ፤ ባህል፣ ወግ እና ታሪካቸውን የሚያከብሩ ስልጡን ዜጎች መኖሪያ ናት፡፡ ጃፓን ማንነትን ከስልጣኔ አስማምቶ የማደግ አይነተኛ ምሳሌ እንደመሆኗ መጠን የመዲናዋ ነዋሪዎች የተረጋጉ፣ ውሸት እና ስርቆትን የሚጸየፉ የሞራል ሰዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ ህዝቡ በአብዛኛው ብዙ አድምጦ ጥቂት የሚናገር ቁጥብ እና አመለ ሸጋ ሲሆን ለእንግዳ ተቀባይነቱም ቢሆን ወደር እንደማይገኝለት ትራቭለርስ ዎርልድ ዋይድ ድረ ገጽ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
ከ37 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት የዓለማችን ትልቋ ከተማ ቶኪዮ የተቆረቆረችው እ.ኤ.አ በ1603 ሲሆን የቀደመ ስሟን “ኢዱ”ን ቀይራ ቶኪዮ የተባለችውም በ1868 ነው፡፡ ቶኪዮ ማለት በጃፓንኛ “የምስራቋ መናገሻ” እንደማለት ሲሆን መዲናዋ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የባህል እና የኪነ ጥበብ መዕከል ሆና ከ4 ክፍለ ዘመን በላይ ለመዝለቅ ችላለች፡፡ ቶኪዮ በውስጧ በምክር ቤት እና በከንቲባ የሚተዳደሩ 23 ጠቅላይ ግዛቶችን አቅፋ ይዛለች፡፡
“የቆሸሸ እጅ ገንዘብ ያመጣል" በሚል ብሂል የሚታወቁት ጃፓናዊያን ጠንካራ የስራ ባህል ያላቸው ህዝቦች ሲሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎችም በእጅጉ ትጉህ ናቸው፡፡ በቀን በአማካኝ 11 ሰዓት በስራ ላይ የሚያሳልፉት “ቶኪዮዎች” ለታታሪነታቸው አብነት የሚሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ምርቶች ያሏቸው ሲሆን ከመኪና ቶዮታ፣ ኒሳን፣ ሱዙኪ፣ ሚትሱቢሺ፣ አይሱዙ እና ሆንዳን፤ ከኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ደግሞ ሶኒ እና ቶሺባን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በመሠረተ ልማት ረገድ ሁሉ ተሰርቶ፣ ተገንብቶ፣ ተዘርግቶ አልቆላታል የምትበለው ቶኪዮ በተለይ የባቡር ትራንስፖርት ስርአቷ በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ የጃፓን ምድር ባቡር (Japan Railway) ቶኪዮ ውስጥ ብቻ ከ800 በላይ መዳረሻ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን ወደ ከተማዋ የሚገቡ እና የሚወጡ ሰዎችን ጨምሮ በቀን ከ30 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያጓጉዛል፡፡ የከተማዋ ባቡሮች አማካኝ የመዘጊያ ጊዜ 18 ሴኮንድ ብቻ መሆኑም ህዝቡ ለጊዜ የሚሰጠውን ከፍ ያለ ዋጋ ያስረዳል፡፡
80 በመቶ የጃፓን መልክዐ ምድር ተራራማ ነው፡፡ በሀገሪቱ ከ18 ሺህ በላይ ተራሮች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ ከ200 የሚበልጡት መገኛቸው ቶኪዮ ውስጥ ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው የመዲናዋ ተራራ ፉጂ ሲሆን 3 ሺህ 776 ሜትር ርዝመት አለው፡፡ ቶኪዮ ከ200 በላይ ደሴቶችንም በውስጧ የያዘች ሲሆን የከተማዋ ጥንታዊነት ከሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ጋር ተዳምሮ ለጎብኚዎች ልዩ ህብር ይፈጥራል፡፡
ቶኪዮ ከ100 የሚበልጡ ሙዚየሞች ያሏት ሲሆን ግዙፉ የቶኪዮ ብሔራዊ ሙዚየም በእድሜ እና በውስጡ በያዛቸው ቅርሶች ብዛት ከሁሉም ይልቃል፡፡ ከ120 ሺህ በላይ ቅርሶችን የያዘው ሙዚየሙ በአመት ከ2 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች የሚጎኙት ሲሆን የሀገሪቷን ታሪክ እና የትውልድ ቅብብሎሽ ቁልጭ አርጎ እንደሚያሳይም ተመስክሮለታል፡፡
የገበያዋ ነገር አይቀመስም የምትባለው ቶኪዮ የውጪ ሀገር ጎብኚዎች ሲሸምቱ ፓስፖርታቸውን በማሳየት ብቻ ከቀረጥ (ታክስ) ነጻ ግብይት እንዲፈጽሙ ማድረጓ ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እና ደጋግመውም እንዲመጡ እንደሚያደርጋቸው ይገለጻል፡፡
መልካም ስነ-ምግባር እና ጨዋነት የጃፓኖች የስልጣኔ መገለጫ እና የሰውነት መለኪያዎች ናቸው፡፡ ይህም ቶኪዮን ሰላም የከተመባት ግብረገብም ከሰማይ ጠቀስ ህንጻዎቿ እና ቴክኖሎጂዎቿ ገዝፎ የሚታይባት ውብ ከተማ አድርጓታል፡፡
በእዮብ መንግስቱ