በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን አቅም በአግባቡ በመጠቀም በአርአያነት የሚጠቀስ ክልል ለመገንባት እንደሚሠራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገልጸዋል።
ርዕስ መስተዳድሩ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራራያ፣ በስድስቱ የክልሉ መቀመጫ ማዕከላት መደበኛ የመንግሥት ተግባራትን በተሟላ መንገድ ለማሰጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራን በማጠናቀቅ ከነገ ጀምሮ በማዕከላቱ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ተቋሟቱን ወደ መደበኛ ተግባር ለማስገባት ጊዜያዊ ቢሮዎችን የመለየት እና የማደረጀት ሥራ መከናወኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት የአመራር ምደባ በማጠናቀቅ የክልል ተቋሟት ሠራተኞችን ወደ ተመደቡበት የክልል ማዕከላት በማጓጓዝ እስከ መሰከረም ወር አጋማሽ መደበኛ መንግሥታዊ አገልገሎቶች በተሟላ መንገድ ወደ ተግባር ይገባሉ ብለዋል።
በስድስቱ መቀመጫ ማዕከላት የሚሰጡ አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማሳደግ ወደ ክልል የሚመጡ ጉዳዮች በአብዛኛው በጥናት ላይ ተመሥርተው በዞን ደረጃ ውሳኔ መሰጠት የሚቻልበት አሠራር እንደሚተገበር አብራርተዋል።
በክልሉ ያለውን አቅም በአግባቡ በመጠቀም በአርአያነት የሚጠቀስ ክልል ለመገንባት ይሠራል ያሉት አቶ ጥላሁን፣ የሰላም ግንባታ፣ ግብርና፣ ማዕድን እና የቱሪዝም ልማት ዘርፎች የክልሉ መንግሥት ዋነኛ ትኩረት መሆናቸውን አንሥተዋል።
ለቆዩ እና አዲስ ለሚነሱ የልማት ፈላጎቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራ ጠቁመው፣ የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎችን በልዩ ትኩረት በመምራት በዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ እና የኑሮ ውድነትን መከላከል እንዲሁ በትኩረት መስክነት የተለዩ ጉዳዮች ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
በሕዝቦች መካከል የቆየው አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች እንደሚጠናከሩ አመላክተዋል።
በሚካኤል ገዙ