በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻው ከ8 ሚሊዮን በላይ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑ ተገለጸ

1 ዓመት በፊት 639
በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻው ከ8 ሚሊዮን በላይ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻው ከ8 ሚሊዮን በላይ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ መስጠፋ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለፁት ለ2015/16 የምርት ዘመን በክልሉ 8.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ከዚህም ዋና ዋና ሰብሎችን ጨምሮ ከ265 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸው በእስካሁኑ ሂደት 8 ሚሊዮን 90 ሺህ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ እጥረትን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ መስጠፋ በተለይም ለደጋማው የክልሉ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ ቅድሚያ እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ስንዴ፣ ገብስ፣ የጥራ ጥሬ ሰብሎችን ጨምሮ በተለያዩ ዘሮች መሸፈኑን ጠቁመው ምርጥ ዘርም በተመሳሳይ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርስ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል በልዋል።

የአፈር ማዳበሪያ እጥረቱን በተፈጥሮ ማዳበሪያ የመተካት ሥራ መሰራቱንና ከ90 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ መስጠፋ ጨምረው አስታውቀዋል።

አንዳንድ አካባቢዎች የፈሳሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አክለው፣ አሲዳማ አፈር ያለባቸውን አካባቢዎች ደግሞ በኖራ የማከም ሥራ ተሰርቶ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በመኸር እርሻው የተያዘውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት አሁንም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በእስካሁኑ ሂደት 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የአፈር መዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱንም በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር ጨምሮ ገልጸዋል።

የምሥራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፋን ተሾመ በበኩላቸው በተያዘው የመኸር አዝመራ በዞኑ 515 ሺህ ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል።

የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ኮምፖስትና ፈሳሽ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን የጠቀሱት አቶ መስፍን በዚህም 500 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከ3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ኖራ በመኸር እርሻው ጥቅም ላይ በማዋል የተፈጥሮ ማዳበሪያ እጥረትን ማካካስ መቻሉን አመልክተዋል።

ከዚህም 256 ሺህ ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ መልማቱን የገለፁት አቶ መስፍን፤ በተመሳሳይ ለውጭ ገበያ የሚሆኑ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች በቴክኖሎጂ ተደግፈው በኩታ ገጠም መልማታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ በተያዘው የምርት ዘመን የመኸር እርሻ 85 በመቶ የሚሆነው በኩታ ገጠም እና በሜካናይዜሽን መልማቱን ገልጸው፤ በዚህም ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top