መቶ ሺዎችን የታደጉት ሥራ ፈጣሪ - በነጋድራስ

6 Mons Ago
መቶ ሺዎችን የታደጉት ሥራ ፈጣሪ - በነጋድራስ

ከ15 ዓመት በፊት መኖሪያ ቤታቸውን እና መኪናቸውን በመሸጥ ባገለገሉ አምቡላንሶች ሥራ የጀመሩት ባለሙያ ዛሬ የትልቅ ድርጅት ኃላፊ እና ባለሀብት ናቸው።

አቶ ክብረት አበበ ቱፋ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሚሠሩበት ወቅት በድንገተኛ አደጋ ወደ ጤና ተቋማት ሳይደርሱ ሕይወታቸውን የሚያጡ በርካታ ሰዎችን ችግር ለመፍታት ፕሮጀክት ቀረፁ። ፕሮጀክቱን ለመጀመር ግን መነሻ ገንዘብ ሊያበድራቸው የፈቀደ ባንክ አልነበረም። እናም የነበራቸውን ቤት እና መኪና ሸጠው ሦስት ያገለገሉ አምቡላንሶች በመግዛት ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ተዘጋጁ።

ነገር ግን በወቅቱ በኢትዮጵያ የግል የድንገተኛ ሕክምና አግልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሀገራዊ መመዘኛ ስላልነበር ፈቃድ ማግኘት አዳጋች ነበር። አቶ ክብረት ግን ለፈተናው ሳይበገሩ ራሳቸው ይህን ስታንዳርድ አዘጋጅተው ያቀረቡት ሰነድ ተቀባይነት አግኝቶ የሥራ ፈቃድ ተረከበው ሥራ ጀመሩ።

ብዙ ፈተናዎችን በፅናት ተሻግረው የመሠረቱት ‘ጠብታ አምቡላንስ’ ዛሬ ከሦስት አሮጌ መኪኖች ወደ 15 ዘመናዊ አምቡላንሶች አሳድጎ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ከአደጋ መታደግ የቻለ ሀገር አቀፍ ድርጅት ሆኗል ይላሉ አቶ ክብረት።

ጠብታ አምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ብቻ ሳይሆን የሥልጠና ማዕከልም ሆኗል። በርካቶችን በቅድመ ሆስፒታል ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት አሠልጥኖ ማስመረቅ ችሏል። አቶ ክብረት አበበ ቱፋ አሁን ደግሞ ወደ ሌላ ታላቅ ባህር ተሻጋሪ ዓላማ ይዘው በመጓዝ ላይ ናቸው። ባገለገሉ መኪኖች የተጀመረው የአምቡላንስ አገልግሎት ወደ አየር ተሸጋግሮ በግል አውሮፕላን ወደሚሰጥ የአየር ላይ አምቡላንስ አገልግሎት ለማሳደግ እየሠሩ ነው።

እኚህ ችግርን በራስ ጥረት በማለፍ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች ታሪክ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑት ሰው፣ አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎችን በማበረታታት እና ለወጣቶች ቅርብ በመሆን ልምዳቸውን በስፋት በማካፈል ላይ ይገኛሉ።

ሁለችንም በተሰማራንበት ሥራ “የኔ ‘ጠብታ’ ምንድን ነው?” ብለን ጠብታችንን ካላዋጣን ራሳችንንም፣ ሀገራችንንም ከድህነት ማውጣት አንችልም!

አቶ ክብረት አበበ ቱፋ በዚህ ሳምንት የነጋድራስ የሥራ ፈጠራ ውድድር ተጋባዥ ዳኛ ሆነው ይቀርባሉ።

ነጋድራስ - የነጋዴዎች ራስ!


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top