የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአፍሪካ እህል በነፃ ለማቅረብ ቃል ገቡ

8 Mons Ago
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአፍሪካ እህል በነፃ ለማቅረብ ቃል ገቡ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን የጥቁር ባሕር እህል ስምምነትን ላልተገባ ጥቅም በማዋል "እፍረት የለሽ" ድርጊት ፈጽመዋል በማለት ወቅሰዋል። 

ፕሬዚዳንቱ ለአፍሪካ ነፃ እህል ለማቅረብ ቃል የገቡ ሲሆን፣ በሀገራቸው እና በአፍሪካ አህጉር መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እ.ኤ.አ. በ2022 ከነበረበት 18 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያድግ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

በሴንት ፒተርስበርግ ከሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በፊት በሰጡት መግለጫ፣ አፍሪካ በቡድን 20 እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንድታገኝ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ከጥቁር ባሕር የእህል ስምምነት መውጣታቸውን አስመልከተው በሰጡት አስተያየት፣ "ምዕራባውያን ስምምነቱን የአሜሪካ እና የአውሮፓ የንግድ ድርጅቶችን ለማበልጸግ ያለ እፍረት ጥቅም ላይ አውለውታል" በማለት ተችተዋል።

አፍሪካን ቢዝነስ እንደዘገበው ከዩክሬን የሚላከው እህል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች እንጂ ለአፍሪካ እና እህሉ ለሚያስፈልጋቸው ሌሎች ሀገሮች እምብዛም እንደማይሄድ ተናግረዋል።

በተጨማሪም እህል እና ማዳበሪያ ወደ ታዳጊ ሀገራት ለመላክ ሩሲያን ከቅጣት ነፃ ከማድረግ ጋር ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መካከል አንዳቸውም ስላልተፈጸሙ፣ የስምምነቱ ሰብዓዊ ዓላማ በዚህ ምክንያት ከሽፏል ብለዋል።

ሩሲያ ለአፍሪካ የምግብ አቅርቦት ሁሌም "ከፍተኛ ትኩረት" እንደምታደርግ፣ እ.አ.አ በ2022 ብቻ 11.5 ሚሊየን ቶን እህል ወደ አህጉሪቱ እንደላከች፣ በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ ደግሞ ከማዕቀብ ጋር እየታገለች ወደ 10 ሚሊየን ቶን የሚጠጋ ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ እህል እንደላከች አበክረው ገልፀዋል።

አክለውም "በሽያጭም ሆነ በነፃ የዩክሬይንን እህልን ለመተካት ሀገራችን ብቃት ያላት መሆኗን ማረጋገጫ መስጠት እፈልጋለሁ፤ በተለይም በዚህ ዓመት ከፍተኛ ምርት ስለምንጠብቅ ይህን እናሳካለን" ብለዋል ፕሬዚዳንት ፑቲን። 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top