ከተለያዩ ከተሞች እና ተቋማት የተውጣጣው የልዑካን ቡድን የካይሮ ከተማን የሕዝብ ብዛት መጨናነቅ ለማስተንፈስ መልሶ የማልማት እና ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን ዘመናዊ፣ ሁለገብ እና ምቹ ከተማን ለመገንባት የተሠሩ ሥራዎችን ጎብኝቷል።
ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት፤ ገጠርን ከከተማ አስማምቶ ለማደግ የተከናወኑ ተግባራትንም ተመልክቷል።
በጉብኝቱ ወቅት ከካይሮ ከተማ አስተዳደር ጋር ከተሞችን በማዘመን፣ ወቅቱን የዋጀ የከተማ እና የመሠረተ ልማት ግንባታን፣ እንዲሁም የተጨናነቁ የከተማ አካባቢዎችን ስለማስተካከል በተሠሩ ሥራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በባህል፣ በታሪክ እና በሕዝብ ብዛት ተቀራራቢነት ያላቸው በመሆኑ የልዑካን ቡድኑ ያገኘው ልምድ በየከተሞቹ ሊተገበሩ የሚችሉ መሆናቸውን አባላቱ ገልጸዋል።
ጉብኝቱ ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግብጽ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተከናወነ መሆኑም ተገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በጉብኝቱ የፌዴራል አመራሮች፣ የአዲስ አበባ፣ የአዳማ፣ የባሕር ዳር እና የሐዋሳ ከተሞች ከንቲባዎችም ተሳትፈዋል።