የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሰማራት ፍላጎት አላቸው፦ ላቲዛ ፒዚ

1 Yr Ago 421
የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሰማራት ፍላጎት አላቸው፦ ላቲዛ ፒዚ

የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው በአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ የጣሊያን ኢንተርፕራይዞች ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ላቲዛ ፒዚ ተናገሩ።

ማኅበሩ በጣሊያን የሚገኙ ዋና ዋና ኢንዱስትሪዎችን፣ ባንኮችን እንዲሁም መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በአባልነት የያዘ ሲሆን፣ በዋናነት አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ይሠራል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ላቲዛ ፒዛ ጋር በጣሊያን ርዕሰ መዲና ሮም ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም በዋናነት በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የጣሊያን ኩባንያዎች ኢንቨስት በሚያደርጉበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይም በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ውስጥ የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎችን ለአብነት የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ ማሻሻያዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግሥት በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን ቱሪዝም እና አይ ሲቲ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም የጣሊያን ኩባንያዎች በተለይ በግብርና ማቀነባበር፣ ማዕድን፣ ኮንስትራክሽን እና ታዳሽ ኃይል ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ ኢንቨስትመንት እና ንግድን ለማሳለጥ ምቹ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

የጣሊያን ኢንተርፕራይዝ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ላቲዛ ፒዚ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እየወሰዳቸው ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎችንም አድንቀዋል።

ይህም የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ስለመሆኑም አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ለጣሊያን ኩባንያዎች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ጠቁመው፣ አሁን ላይ በርካታ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ ማኅበሩ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በቀጣይነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ማኅበሩ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጨምረው ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top