የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የንግድ ኮሪደር ሥር-ነቀል የማሻሻያ እድሳት ሊደረግለት እንደሆነ ተገለጸ

1 Yr Ago
የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የንግድ ኮሪደር ሥር-ነቀል የማሻሻያ እድሳት ሊደረግለት እንደሆነ ተገለጸ

ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ቀንድ ግንኙነት እና የንግድ መከፈት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተነገረለት ይህ የማሻሻያ እድሳት የሚከናወነው በቅርቡ በፀደቀው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሸቲቭ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት አማካይነት ነው።

ፕሮጀክቱ ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ባበረከተው የ730 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚተገበር መሆኑንም የዓለም ባንክ ገልጿል።

ፕሮጀክቱ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው ተብሏል።

ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ማጠናከር የኢትዮጵያን እምቅ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ይገልጻሉ።

ለ120 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዋነኛ የንግድ መተላለፊያ መስመር የሆነው ይህ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት ቀጣናዊ ውህደትን እና አካታች ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ይላሉ ሚኒስትሩ።

ዕድገቱን በማስቀጠል ከዚያ የሚገኙ የሰላም ትሩፋቶችን ማጣጣም እንዲቻል በሙሉ ትኩረት እየሠራን ነውም ብለዋል።

95 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ገቢ/ወጪ ንግድ በአዲስ አበባ-ጅቡቲ ኮሪደር በኩል ይተላለፋል።

ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክቱ በተለይ ከሚኤሶ-ድሬዳዋ ያለውን መንገድ ለማዘመን እና ለማስፋፋት ይውላል።

ይህም በኮሪደሩ የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ብቃት በማሻሻል የሀገሪቱን የንግድ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው የዓለም ባንክ መረጃ ያትታል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top