ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካ ሀገራት የተጋረጠባቸውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ታሳቢ ያደረገ የአሰራር ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

1 Yr Ago
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካ ሀገራት የተጋረጠባቸውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ታሳቢ ያደረገ የአሰራር ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካ ሀገራት የተጋረጠባቸውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ታሳቢ ያደረገ የአሰራር ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የባለብዙ ወገን ልማት ባንኮችን ሞዴል ማሻሻል" በሚል ርዕስ በፓሪስ በተካሄደ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።

በባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ሊደረግ ስለታቀደው ማሻሻያ አስተያየታቸውን የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ታዳጊ ሀገራት በተለይም የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ውስብስብ ቀውሶች እንደተደቀኑባቸው ገልፀዋል።

ሀገራቱ በተለይ ከገንዘብ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከዕዳ ጫና፣ ከኑሮ ውድነት እና ከሰላም እጦት ጋር በተያያዙ ቀውሶች እየፈተኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ በአፍሪካ የችግሮቹ ስፋት፣ ጥልቀት እና ውስብስብነት አሳሳቢ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፣ የዋጋ ግሽበቱ በሁሉም ሸቀጦች ላይ በሚባል ደረጃ በእጅጉ ከማሻቀቡ የተነሳ፤ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የዕለት ጉርስ ማግኘት ፈታኝ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

በእነዚህ ሀገራት የግሉ ዘርፍ እና የመንግሥት ዕዳም ከምን ጊዜውም በላይ የተከማቸ በመሆኑ፤ መንግሥታቱ ከልማት ሥራ ይልቅ በዕዳ አስተዳደር ተጠምደው ይገኛሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ በሀገራቱ ላይ እያደረሰው ያለው አሉታዊ ተፅዕኖም የከፋ ነው።

እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ለመሻገር ሀገራቱ ከፍተኛ ሀብት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፤ እንዲያውም በተቃራኒው ከበለፀጉ ሀገራት ያገኙት የነበረው ብድር እና ድጋፍ ሲቋረጥባቸው ይስተዋላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ እነዚህ ሀገራት የተጋረጠባቸውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ መሻገር እንዲችሉ፤ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ ይህን ታሳቢ ያደረገ የአሰራር ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ በፊት ቃል የተገቡ ስምምነቶችን መተግበር፣ የኮንሴሽናል ፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ፣ ወደ አረንጓዴ ልማት ለሚደረገው ሽግግር አስፈላጊውን ድጋፍ መመደብ፣ የዕዳ ቀውስን ማቆም እና ሌሎች ገንቢ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳስበዋል።

አረንጓዴ ልማትን በፋይናንስ መደገፍ እንደሚገባ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ 98 በመቶ የኃይል አቅርቦቷን የምታመነጨው ከታዳሽ የኃይል ምንጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯ አማካይነት እስካለፈው ዓመት ብቻ 25 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞችን መትከሏን፣ በተያዘው ክረምት 7 ቢሊዮን ተጨማሪ ችግኞችን በመትከል ላይ መሆኗን እና በቀጣይ 3 ዓመታት ይህን ቁጥር ወደ 50 ቢሊዮን ለማድረስ መታቀዱንም አብራርተዋል።

በዚህም ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለ1 ችግኝ በአማካይ 1 ዶላር፣ በአጠቃላይ ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯ ደግሞ ከ50 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ፈሰስ እያደረገች መሆኗንም አመላክተዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top