14ኛው የኢጋድ መሪዎች መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

1 ዓመት በፊት 498
14ኛው የኢጋድ መሪዎች መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

14ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) መሪዎች መደበኛ ጉባኤ በጅቡቲ መካሄድ ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎችና ተወካዮቻቸው በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።

በቀጠናው ሠላምና ደህንነት እንዲሁም በሀገራቱ የልማት ስራዎች ላይ ባተኮረው ስብሰባ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የኢጋድ አባል ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ በመክፈቻ ንግግራቸው አሳስበዋል።

የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት መፍታት ተገቢ መሆኑን ያነሱት ዋና ፀሐፊው፤ ኢትዮጵያ ሰላሟን ለመመለስ ያሳየችው ቁርጠኝነት ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢጋድም የቀጠናው ሀገራት ዘላቂ ሰላምን እንዲያረጋግጡ የሚያከናውናቸውን ተግባራትና ድጋፍ አጠናክሮ  እንደሚቀጥል ዶ/ር ወርቅነህ ገልጸዋል።

የቀጠናው አንዷ ሀገር የሆነችው ሱዳን ከገባችበት የሰላም እጦት እንድትወጣም የኢጋድ አባል ሀገራት በትብብር መስራት ይገባቸዋልም ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሐመት በበኩላቸው፥ ሱዳን ችግሮቿን ለመፍታት ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ መከተል እንደሚገባት ተናግረዋል።

በጉባኤው የኢጋድ አባል ሀገራት በአፍሪካ የተከሰቱ ለውጦችን ለመገምገምና እና በቀጠናው ዘላቂ ልማትን ለማስመዝገብ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ይወያያሉ ተብሏል።

ውይይቱ በአባል ሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር፣ ቀጠናዊ ውህደትን ማጎልበት፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ የኢኮኖሚ እድገትና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።

በሮዛ መኮንን


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top