በሸገር ከተማ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ደረጃውን የጠበቀ ህጋዊ የመስጂድ መስሪያ ቦታ እንደሚሰጥ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተስማምተናል - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት

1 Yr Ago
በሸገር ከተማ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ደረጃውን የጠበቀ ህጋዊ የመስጂድ መስሪያ ቦታ እንደሚሰጥ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተስማምተናል - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት
በሸገር ከተማ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ደረጃውን የጠበቀ ህጋዊ የመስጂድ መስሪያ ቦታ እንደሚሰጥ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ጋር በተደረገ ውይይት ከስምምነት መደረሱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለፀ።
በውይይቱ ላይም የክልሉ መንግስት ከህግ አግባብ ውጭ የተሰሩትን መስጂዶች በራሱ ከማፍረስ ይልቅ የሌሎች እምነት ተቋማትን ጨምሮ ምክክር በማድረግ ራሳቸው ቤተ እምነቶቹ እንዲያፈርሱ በውይይቱ ላይ መነሳቱ ተገልጿል።
በሸገር ከተማ አስተዳደር 800 የሚሆኑ የተለያዩ የእምነት ተቋማት ቢኖሩም፣656 የሚሆኑት ከፕላን ውጭ የተሰሩ መሆናቸው ተገልጾ፤ በፕላኑ መሰረት ለእምነት ተቋማቱ የሚመጥኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ቦታዎች እንደሚሰጥ በውይይቱ መነሳቱንም ምክር ቤቱ ጠቁሟል።
እስካሁን ምንም አይነት ምክክር ሳይደረግ 22 መስጂዶች በሸገር ከተማ መፍረሳቸውን ተከትሎ ብጥብጥ እንዲነሳ እና ለሰላማዊ ዜጎች ሞት ምክንያት መሆኑም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
በመሆኑም ጠቅላይ ምክር ቤቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች እየሰራ እንደሆነ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ህዝበ ሙስሊሙ በነገውም ሆነ በቀጣይ ጁምዓዎች ምንም አይነት ተቃውሞ አለመኖሩን በመገንዘብ እና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ጁምዓ ሰግዶ እዲመለስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት አሳስቧል።
በአቤል ሙሉጌታ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top