ለዘንድሮ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል - ግብርና ሚኒስቴር

11 Mons Ago
ለዘንድሮ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል - ግብርና ሚኒስቴር

ለ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በመርሐ-ግብሩ ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም አስታውቋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን በሚኒስቴሩ የስነ-ሕይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃና ጥምር ደን እርሻ ዴስክ ኃላፊ አቶ ብስራት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለመርሐ ግብሩ የዘር ዝግጅት ተከናውኖ 116 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል።

በችግኝ ዘር ዝግጅትም 60 ከመቶ የሚሆነው ለአገር በቀል ደን፣ የተቀረው ለጥምር ግብርና፣ ለፍራፍሬና ሌሎች ምርቶች መሆኑን ጠቁመዋል።

በሕብረተሰብ ተሳትፎ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ለችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ዝግጅት ላይ መሳተፉን ተናግረዋል።

በአራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ቆይታ 1 ሚሊዮን 700 ሺህ በሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ 775 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ተደርገው መከለላቸውን ገልጸዋል።

በ2014 ዓ.ም በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሸፈነ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበት እንደነበር የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በ2014 ዓ.ም ከተተከሉት ችግኞች መካከል 93 በመቶ የሚሆነው  እንክብካቤ ያገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 88 ነጥብ 7 ከመቶ በተደረገው እንክብካቤ መፅደቁን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 17 ከመቶ መድረሱንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top