ለሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ ተጠየቀ

11 Mons Ago
ለሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ ተጠየቀ

በአረንጓዴ አሻራ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ተግዳሮቶችን በማረም ለሁለተኛው ምዕራፍ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ ተጠየቀ።

ያለፉትን ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዎች ለማስቀጠል ባለድርሻ  አካላት ልምዳቸውን፣ ዕውቀታቸውን  እና ክህሎታቸውን የሚያካፍሉበት የፓናል ውይይት በግብርና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀልበስ አቅዶ ተግባራዊ ካደረጋቸው የተለያዩ ኢኒሼቲቮች አንዱ ማህበረሰብን ያሳተፈ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ነው ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ በዚህም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎችን ማከናወን ባህል እየሆነ ከመምጣቱ ባለፈ ተጨባጭ አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውጤቶች ተመዝግበውበታል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢኒሼቲቩ የወል ተፋሰሶች እንዲያገግሙ፤ የአፈር መከላት እንዲቀንስና ለምነቱ እንደጨምር፤ የእፅዋት ሽፋን፣ የገፀ እና ከርሰ ምድር ውሃ መጠን፣ የሰብልና የእንስሳት ምርታማነት እንዲያድግ፤ እንዲሁም የአርሶ  አደሩ ገቢ እንዲሻሻል ማድረግ ተችሏልም ብልዋል ሚኒስትሩ።

በመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ኢትዮጵያ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትክል በመቻሏ በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይ ከመርሐግብሩ በፊት የነበረውን የተጨፈጨፈ ደን ሽፋን ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 32 ሺህ ሄክታር፣ በየዓመቱ ይሸረሸር የነበረውን አፈርም ከ130 ሺህ ቶን ወደ 42 ሺህ ቶን መቀነስ፣ ለ900 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በመርሐግብሩ ያገኘችውን ስኬትና ተሞክሮ ለሳውዲ አረቢያና ለሌሎች የመካከኛው ምሥራቅ ሀገራት እንድታካፍል ተጠይቃለች ብለዋል።

ለመርሐግብሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስኬታማነት የእውቀት፣ የፋይናንስም ሆነ የቴክኒክ ድጋፍ ያደረጉ አካላት በቀጣዩ ሁለተኛ ምዕራፍም ይህንኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተፈጥሮ ሀብትን እየተንከባከቡ በማልማት  እና የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርና ልማትን በማሳለጥ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተተለመ ኢኒሼቲቭ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጀመረችው ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ በመጀመሪያው  ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በገበታ ለሀገር፣ በሌማት ትሩፋትና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።

ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ  አሻራ መርሐግብርን ለማሳካትም በመጀመሪያ ምዕራፍ የተገኙ ውጤቶችን በማብዛት እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ መረጃ አያያዝ በማገዝ ለስኬቱ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በፓናል ውይቱ ላይ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የቀጠናው የዓለም ባንክ ተወካይ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ተጠሪዎች ተገኝተዋል።

በዘአማኑኤል መንግሥቱ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top