የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ጋር በተያያዘ በቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች ላይ ግፊት ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተገለፀ

341 Days Ago
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ጋር በተያያዘ በቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች ላይ ግፊት ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተገለፀ

የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች የዘንድሮ ስብሰባቸውን ወደሚያደርጉባት የጃፓኗ ሂሮሺማ ከተማ እየገቡ ነው።

የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት እና የቻይና-ታይዋን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ከኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ጋር በተያያዘ መሪዎቹ ላይ ግፊት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል ተብሏል።

እንደ ዘ ጋርዲያን ዘገባ፥ እ.ኤ.አ. በ2016 የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሂሮሺማን መጎብኘታቸውን ተከትሎ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያን የመቀነስ አጀንዳ እንደ አዲስ ተነስቶ ነበር።

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በምዕራበውያን ጫና ምክንያት በዩክሬን ታክቲካል የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውል በይፋ ለመቃወም ፈቃደኛ አለመሆናቸው እና ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ሊደርሱ የሚችሉ የተራቀቁ ሚሳኤሎችን መሥራት መቀጠሏ የጃፓኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አሳስቧቸዋል።

ኪሺዳ በቅድመ ጉባኤው ንግግራቸው "ዓለምን ከኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ነፃ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ ተሞክሮ ማቅረብ እና እውነታውን በትክክል ማስተላለፍ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ለዚህ ደግሞ ከኛ በላይ ምስክር የለም" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው ሰሞኑን ሂሮሺማን ከመጎብኘታቸው በፊት ለጃፓን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃል "ይህ ወቅት በተለይም የኒውክሊየር ትጥቅ ማስፈታት አስፈላጊነት ላይ አጥብቀን የምንነጋገርበት ነው" ብለዋል።

ሂሮሺማ ላይ ከተጣለው ቦንብ የተረፉት የ80 ዓመቱ አዛውንት ሺግኪ ሞሪ በበኩላቸው "መሪዎቹ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ ሲወስኑ ማየት እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን በቀላሉ እዚህ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ብዬ አላምንም" ብለዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ዋሽንግተን በኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ላይ ገለልተኛ አጀንዳ ማራመድ እንደማትፈልግ ሲናገሩ፣ የጀርመን መንግሥት ከፍተኛ ምንጮች ደግሞ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ማስፈታት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፣ ነገር ግን "በዋነኛነት ለጃፓን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

የ2023 የቡድን 7 አባል ሀገራት መሪዎች ስብሰባ እ.ኤ.አ ከሜይ 19 እስከ 21 በጃፓኗ ሂሮሺማ ከተማ ይካሄዳል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top