በጦርነቱ የተጎዱ 6 ድልድዮች ተጠግነው ለትራፊክ ክፍት ሆነዋል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

10 Mons Ago
በጦርነቱ የተጎዱ 6 ድልድዮች ተጠግነው ለትራፊክ ክፍት ሆነዋል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

በጦርነት አካባቢዎች ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት የደረሳባቸው ስድስት ድልድዮች ከ173 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ጥገና ተደርጎላቸው ለትራፊክ ክፍት መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይና ስትራክቸር ስራዎች ዳይሬክተር ኢንጅነር ጌትነት ዘለቀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ድልድዮች እየተጠገኑ ለትራፊክ ክፍት እየተደረጉ ናቸው።

በአሁኑ ጊዜም በጦርነቱ ከተጎዱ ድልዮች ስድስት የሚሆኑት ጥገናቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ተደርገዋል።

ጥገና የተደረገላቸው ድልድዮች ከወልድያ በ10 ኪ.ሜ ላይ የሚገኘው አለውሃ ድልድይ፣ በጭፍራ ወልድያ መንገድ ላይ የሚገኘው ጨረቲ ድልድይ፣ በቆቦ አካባቢ የሚገኘው ጎቡ ድልድይ፣ ከሰቲት ሁመራ ወደ ሽሬ የሚወስደው ተከዜ 3 ድልድይ እና ተከዜ ድልድይ እንዲሁም ከኮረም ሰቆጣ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ጸላርይ ድልድይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ጊዜም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስት ድልድዮች በየአካባቢው ባሉ የመንገዶች አስተዳደር ቅርንጫፎች ሪፖርት ተደርገው እነሱን ለመጠገን ግብዓት እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ድልድዮች በአላማጣና በመቀሌ የሚገኙ ሲሆኑ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጥገናቸው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚደረጉም ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top