“ለሰላም ሁሉንም እናደርጋለን፤ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ እናጠናክራለን” - አቶ ጌታቸው ረዳ

7 Mons Ago
“ለሰላም ሁሉንም እናደርጋለን፤ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ እናጠናክራለን” - አቶ ጌታቸው ረዳ
ለሰላም ሁሉንም እናደርጋለን ፣ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ እናጠናክራለን፣ ክልሎችም ይህን ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ 'ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና’ በሚል መሪ ሐሳብ የምስጋና እና የዕውቅና ሥነ ስርዓት እየተካሔደ ነው።
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በስምምነቱ መሠረት ሕዝቡን እና ክልሉን የሚጠቅሙ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
ለስምምነቱ በፍጥነት መተግበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላሳዩት ከፍተኛ ድፍረት የተሞላበት ቁርጠኝነት በትግራይ ሕዝብ ስም እናመሰግናለን ብለዋል።
ቀሪ ሥራዎችም በተያዘው ፍጥነት ልክ እንዲከናወኑ ሲሉ ጠይቀዋል።
ከትግራይ ሕዝብ የፍቅርና የሰላም መልዕክት ይዤ መጥቻለሁ ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ሰልችቶታል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በትናንትናው ዕለትም የሕዝብ ትራንስፖርት በአፋር በኩል መጀመሩን ጠቁመው፣ ይኸው አገልግሎት በአማራ ክልል በኩል እንዲጀመርም በጋራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመጨረሻም፣ ከይዋጣልን መንፈስ ወጥተን የፍቅር የስራ ቋንቋ መጀመር አለብን፤ ሰላም እንዲፀና የትግራይ ክልል ጊዚያዊ መንግስት የበኩሉን ይሰራል ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top