ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት የሰረቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በየካ ክፍለ ከተማ ወራዳ 9 ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው መብራት ኃይል ግቢ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።
ንብረትነቱ የቻይና ፓወር ኮንስትራክሽን የሆነ እና በግቢው ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ከ5 ሚሊዮን 9 መቶ ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው የኤሌክትሪክ ሽቦ ማገናኛ ብረት በቻይና ፓወር ኮንስትራክሽን ሠራተኞች ተሰርቆ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት የደረሰው የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል ወንጀሉን ፈፅመዋል የተባሉትን አንድ የድርጅቱን ሾፌር እና 2 የጉልበት ሠራተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከተያዙ በኋላ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ሥራም ንብረቶቹን ለሥራ የተፈለጉ በማስመሰል በተሽከርካሪ ጭነው ካወጡ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ በመውሰድ አንዱን ኪሎ በ40 ብር ሂሳብ በአጠቃላይ በ64 ሺህ ብር ለአንድ ግለሰብ እንደሸጡ ተረጋግጧል።
የተሰረቀውን ንብረት በማስመለስ እና ንብረቶቹን የገዛውን ግለሰብ ጨምሮ በአጠቃላይ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የምርመራ ሥራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ለመሠረተ ልማት አገልግሎት የሚውሉ ንብረቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የሚገቡ በመሆናቸው በእነዚህ ንብረቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ እና በሕዝብ ተጠቃሚነት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለማስቀረት ኅብረተሰቡ በወንጀል መከላከል ሥራው ላይ ለፀጥታ አካላት እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።