የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሶማሊያ ባይደዋ ከተማ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎበኙ

11 Mons Ago
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሶማሊያ ባይደዋ ከተማ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎበኙ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት /ተመድ/ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሶማሊያ ባይደዋ ከተማ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎብኝተዋል።
በዕለቱ የሴክተር ሦስት አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል በስፋት ፈንቴ፣ የባይደዋ ከተማ ከንቲባ አብዱላሂ አሊ ዋቲ እና የክልሉ የፓርላማ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ሻምሶ መሀመድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከጉብኝቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ በሶማሊያ ያለው ድርቅ በኅብረተሰቡ ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ጉብኝቱ ሰብዓዊ ውይይቶችን ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት የቀጠናውን ፀጥታ ከማስፈን በተጨማሪ የድርጅቱን ሠራተኞች ደኅንነት በተገቢው በመጠበቅ እና ከእኛ ጋር ሥራዎችን በማከናወናቸው ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሴክተር ሦስት አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል በስፋት ፈንቴ፣ ዋና ጸሐፊውን በመቀበል በአካባቢው የሚገኘውን የስደተኞች መጠለያ ካምፖችን እና የተፈናቀሉ ዜጎችን በመዘዋወር ማስጎብኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ሴክተሩ አሸባሪው አልሸባብ ጥቃት እና ጉዳት እንዳያደርስ አትሚስ የሰጠውን አህጉራዊ ተልዕኮ ያለምንም መዘናጋት ግዳጁን በአግባቡ በመፈፀም ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top