የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

1 Yr Ago
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
 
በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው በፌዴራል መንግሥት የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን በአፈጻጸም ሲያጋጥሙ የነበሩ እና ለመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ የአሠራር ጉድለቶችን ለማረም፣ የተቋማትን ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የሚያጎለብት፣ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓታችን በቴከኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እንዲሁም የአገር ውስጥ አምራቾች በመንግሥት ግዢዎች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማገዝ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶች በማከል እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ረቂቅ ደንብ ላይ ነው። በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አዋጅ ቁጥር 1273/2014 ጠቅለል ባለ መልኩ የተደነገጉ ጉዳዮችን በተለይም የፋይናንስ ጉድለት አሸፋፈን፣ የስጋት መቀነሻ ስልቶች እና በተለያዩ እርከኖች ሊኖር የሚገባውን የቋት ክፍፍል በሚመለከት በዝርዝር መደንገግ በማስፈለጉ፣ አዋጁን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የአፈጻጸም ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ የመድኅን ሥርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን ምከር ቤቱም በደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ሌላው ምከር ቤቱ የተወያየው በማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። ማዕድናት የማይታደሱ የተፈጥሮ ሀብቶች በመሆናቸው መጭውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል፣ በአካባቢ ጥበቃ መርሆዎች ላይ የተመሰረተና ከስነ-ምህዳር ጋር የሚጣጣም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ የሆነ የማዕድን ሁበት አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓት የሚዘርጋ፣ ከውጭ የሚገቡ የማእድን ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት፣ ውጭ በመላክ የሚገኝ የዉጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያግዝ፣ በአጠቃላይ ለአገራችን ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውን አስተዋጾ ማሳደግ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምከር ቤት ቀርቧል። ምከር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top