የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ ነው - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

1 Yr Ago
የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ ነው - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አሁን ወደ ተግባር የገባው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፣ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ባሉ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ አስፈላጊነት ከመግባባት ላይ በመደረሱ እንዲሁም አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሰላም ከዚህ ቀደሙ የተሻሻለ በመሆኑ እና ይህንን ትልቅ ተልዕኮ ለማስፈጸም በሚያስችል መልኩ መሆኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስራዎቹ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ሰራዊቱን የማጠናከር እና የማደራጀት ሥራው በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የክልል ልዩ ኃይሎች በተለያዩ መዋቅሮች እንዲደራጁ የሚያስችላቸው ተግባራዊ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ባስቀመጠው አማራጭ መሰረት የልዩ ሀይሉ ፍላጎት እና ምርጫ ተከብሮለት የመልሶ ማደራጀት ስራው የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል አንደኛው አማራጭ ሲሆን ይህም ትልቅ አገራዊ ጥሪ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ሌላው የክልሉን የፖሊስ ሀይል መቀላቀል ወይም ወደ መደበኛ ኑሮው መመለስ የሚሉ አማራጮች የቀረቡ ሲሆን ወደ ሲቪል ለሚመለሱ የማቋቋሚያ በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል፡፡
የክልል ልዩ ሀይልን መልሶ የማደራጀት ሂደት በአንዳንዶች ዘንድ ግልጽ ባለመሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎች እየወጡ ስለመሆናቸውም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡
የክልል ልዩ ሀይልን መልሶ የማደራጀት ሂደት በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ እየተከናወነ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ትጥቅን ከማስፈታት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጸው፤ ይህንን ሂደት ትጥቅ ከማስፈታትጋር በማያያዝ የተለያዩ ውዥንብሮችን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ፍጹም የተሳሳተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከህወሓት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረትም በተቀመጠለት መርሃ ግብር ታጣቂ ሀይሉ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የክልል ልዩ ሀይልን መልሶ የማደራጀት መርሃ ግብር በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በመግባባት ጭምር የሚከናወን መሆኑን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top