በካፒታል ገበያ ለሚሳተፉ ተዋንያን ከሶስት ወር በኋላ ፈቃድ መስጠት ይጀመራል ፡ - የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን

8 Mons Ago
በካፒታል ገበያ ለሚሳተፉ ተዋንያን ከሶስት ወር በኋላ ፈቃድ መስጠት ይጀመራል ፡ - የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን
የኢንቨስትመንት ባንኮችን ጨምሮ በካፒታል ገበያው ለሚሳተፉ የዘርፉ ተዋንያን ከሶስት ወር በኋላ ፈቃድ መስጠት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ባለስልጣኑ ቦርድና ኃላፊ ተሹሞለት ወደ ስራ በገባባቸው ሶስት ወራት በርካታ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ አዲስ እንደመሆኑ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት፣ በገበያው ላይ ለሚሳተፉ የዘርፉ ተዋንያን ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር የካፒታል ገበያን ጽንሰ ሀሳብ፣ ጥቅሙንና እንዴት እንደሚሰራ ብሎም በገበያው የሚሳተፉ አካላት እንዴት መግባት እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በካፒታል ገበያው ለሚሳተፉ ኢንቨስተሮች፣ ደላሎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ከሶስት ወራት በኋላ በካፒታል ገበያ የሚያሳትፋቸውን የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ መስጠት እንጀምራለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ስርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት የሚያጠናክር የካፒታል ገበያ 'በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013' ተቋቁሟል።
በዚህ አዋጅ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ "የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን" መስሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top