የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪቶችን ህገወጥ አካሄድ ለማስቀረት የኦንላይን አሰራር መተግበር ተጀምሯል ፡- የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር

1 Yr Ago
የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪቶችን ህገወጥ አካሄድ ለማስቀረት የኦንላይን አሰራር መተግበር ተጀምሯል ፡- የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር
በመንግስት በሚደረጉ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪቶች ላይ የሚታዩ ህገ ወጥ አሰራሮችን ለማስቀረት በኦንላይን አንዲፈፀም መደረጉን የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡
የስራ ስምሪቱን ከምዝገባው ጀምሮ በቴክኖሎጂ በማገዝ ከሰው ንክኪ ነፃ በማድረግ ህገ ውጥነትን ለማስቀረት የተጀመረ ስራ ውጤት በማሳየት ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ አበበ ዓለሙ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰፊ የአሰራር ማሻሻያ ከተደረገባቸው የስራ ክፍሎች መካከል የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ዘርፍ አንዱ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን አማራጭ የስራ እድል ለመጠቀም ዓለም አቀፍ የስራ ገበያን የሚያፈላልግ የስራ ክፍል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ሀላፊው ጠቁመዋል፡፡
እስካሁንም የስራ ስምሪት ለማድረግ ስምምነት ከተደረሳበቸው ሀገራት መካከል ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ጆርዳን እና የተባበሩት ኤሜሬትስ እንደሚገኙበት አቶ አበበ አስረድተዋል፡፡
በቅርብ ጊዜያት ደግሞ ከኩዬት፣ ባህሬን፣ ጀርመን እና ሌሎች ሀገራት መንግስታት ጋር ስምምነት በመፈፀም ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰማሩ እና ከራሳቸው አልፎ ሀገርን የሚጠቅሙበት ሂደት እንዲዘረጋ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በተዘረጋው የኦን ላይን ስርዓት አማካኝነት ስምምነት በተፈጸመባቸው ሀገራት በህጋዊ መንገድ መስራት የሚፈልግ ሰው አጠቃላይ መረጃው በስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የተመዘገበ እና የተረጋገጠ በመሆኑ ከማንኛውም የህገወጥ እንቅስቃሴ የሚከላከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም በዋናነት በመረጃ ቋት ውስጥ የታቀፉ ዜጎችን የጣት፣ የእጅ እና የፊት አሻራ እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን ያካተተ መሆኑንም ነው ስራ አስፈፃሚው የጠቀሱት፡፡ የስራ ስምሪቱ ከመዳረሻ ሀገራት የስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች እና በየሀገራቱ ካሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በኦንላይን የሚተሳሰር በመሆኑም የሚፈጠሩ ችግሮችንም በአግባቡ ለመፍታት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ጊዚያት በተለያዩ ሙያዎች በከፊልና በተሟላ ሁኔታ የሰለጠኑ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደተለያዩ ሀገራት መላካቸውን የጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው፤ እስካሁን ባለው ሂደት መልካም ውጤት መታየቱን ተናግረዋል፡፡
ለስራ ወደ መዳረሻ ሀገራት የሚደረግ እንቅስቃሴ በሶስት መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ የሚገልፁት አቶ አበበ፤ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በውጭ ሀገር ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ በግል የሚደረጉ የስራ ስምሪቶች አንዲሁም የመንግስት የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባስቀመጠው አቅጠጫ መሰረት ከዚህ በኋላ በመንግስት የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ከሃገር ወጥተው መስራት የሚፈልጉ ዜጎች የስልጠና እና የሙያ ብቃት መመዘኛ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉ እንደሚደረግም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በቀጣይም 100ሺህ የሚጠጉ የሰለጠኑ ዜጎችን በውጭ አገራት የስራ ስምሪት ለማከናወን መንግስት ሂደት ላይ መሆኑ መግለፁም የሚታወስ ነው።
በይስሃቅ ታሪኩ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top