የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 90 በመቶ መጠናቀቁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ

1 Yr Ago
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 90 በመቶ መጠናቀቁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 90 በመቶ መጠናቀቁን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ።
የሕዳሴ ግድብ መሠረተ ድንጋይ የተጣለበት 12ኛ ዓመት የቦንድ ሳምንትን አስመልክቶ ጽ/ቤቱ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ሴት ነጋዴዎች ማኅበር እና ሌሎች ማኅበራት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ለግድቡ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ የፖለቲካ ልዩነት፣ ዕድሜ እና ጾታን ሳይገድብ የተደረገ መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሓ ገልጸዋል።
አሁንም የሕዝብ ድጋፋን ለማስቀጠል የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
የግድቡ ግንባታ በዜጎች ዘንድ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ፣ የፍትሕ ሚዛን የታየበት የኅብረት ተሳትፎ የተስተዋለበት ነው ያሉት ደግሞ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ተካ ናቸው።
ዳይሬክተሩ አክለውም ከብር ድጋፋ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን በመመከት ረገድ ዳያስፖራው ላደረገው አስተዋፅኦ አመስግነው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በ12 ዓመታት ውስጥ 17.7 ቢሊዮን ብር ከኅብረተሰቡ የተሰበሰበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 15.5 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበላይነት የማስተዳደር ሥራ መሥራቱን የባንኩ ዳይሬክተር ዳዊት አማረ ገልጸዋል።
የቦንድ ሳምንቱ በፓናል ውይይት፣ በሥነ-ጽሑፍ ምሽት እንዲሁም በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር ሲሆን በመጪው ቅዳሜ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይፋዊ የመክፈቻ ፕሮግራም የሚደረግ ይሆናል።
በፍሬሕይወት ረታ
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top