ኮንትሮባንድ ለኢኮኖሚው እድገት ትልቅ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ህገወጥነትን መከላከል ይገባል - አቶ ደመቀ መኮንን

1 Yr Ago 317
ኮንትሮባንድ ለኢኮኖሚው እድገት ትልቅ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ህገወጥነትን መከላከል ይገባል - አቶ ደመቀ መኮንን

ኮንትሮባንድ ለኢኮኖሚው እድገት ትልቅ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ህገወጥነትን መከላከል ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት "የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሀገራዊ ቅንጅት" በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን እንደገለጹት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊ ነው።

"የምናመርተውን ምርት በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ጐረቤት ሀገራት እንዳይሄድ መቀጣጠር፤የንግድ ስርአታችንን የማዘመን ስራ መስራት" ይገባል ያሉት አቶ ደመቀ፤ ኮንትሮባንድ ለኢኮኖሚው እድገት ትልቅ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ህገወጥነትን መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት የክልል መሪዎች በተቀናጀ መልኩ መስራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ኢኮኖሚውን በስርአትና በቅንጅት መምራት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ጠቃሚ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ "ህዝባችንን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት መቀነስ ይገባል።

የውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ኢኮኖሚውን ማነቃቃትና የኮንትሮባንድን እንቅስቃሴን ለመግታት የሚያስችል የቅንጅት ስራ መስራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

የመድረኩ ዓላማ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም፣ የወጭ ንግድ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በተቀናጀ መልኩ መገምገምና አቅጣጫ ማስያዝ ነው።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ አምባሳደሮች፣ የውጭ አጋር ድርጅቶች፣ የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዥ፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከንቲባ፣ ሚኒስትሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top