የደም ማነስ በሽታ

1 Yr Ago
የደም ማነስ በሽታ

የደም ማነስ በሽታ የሚከሰተው በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ቀይ የደም ህዋሳት ቁጥር ሲያንስ ወይም በውስጣቸው የሚገኘው ሄሞግሎቢን የሚባለው ሞሎኪውል መጠን ሲያንስ ነው።
ቀይ የደም ህዋሳት በደማችን ውስጥ ከሚገኙ ብዙ አይነት ሌሎች ህዋሳት አንደኛው ሲሆኑ ዋነኛ ስራቸው በደም ስራችን ውስጥ ኦክስጅንን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ነው። ሁሉም የሰውነት ክፍሎቻችን ይህንን ኦክስጅን ከምግብ የምናገኘውን ንጥረ ነገሮች ወደ ኃይል (ጉልበት) ለመቀየር ይጠቀሙበታል።
ስለዚህ የደም ማነስ በሚኖርበት ጊዜ የሰውነታችን ህዋሳት በሙሉ በቂ ኃይል ስለማያገኙ ድካም ፣ አቅም ማጣት እና የመሳሰሉ ምልክቶች ይስተዋላል።
የደም ማነስ ህመም ብዙ ሰዎችን ያጠቃል። ይሄ ችግር በተለይ እንደኛ ሀገር ባሉ ታዳጊ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ላይ በብዛት ይታያል። ህፃናት፣ እርጉዝ ሴቶች እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። እንደ ዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት መረጃ በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች 25% የሚደርሱት ወይም ከአራቱ አንዱ ሰው የደም ማነስ በሽታ እንዳለበት ‘የጤና ወግ’ የተሰኘው ድረ ገፅ መረጃ ያመለክታል። ይህም ወደ 1.62 ቢሊየን ሕዝብ ማለት ነው።
የደም ማነስ በምን ምክንያት ይፈጠራል?
1 ሰውነታችን በቂ የሆነ ቀይ የደም ሴል (ህዋሳት ) ሳያመርት ሲቀር
2 ቀይ የደም ህዋሳት በተለያዩ ምክንያቶች ቶሎ ቶሎ የሚሞቱ ከሆነ
3 የደም መፍሰስ

የደም ማነስ ምልክቶች
የደም ማነስ በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጣ ስለሆነ ምልክቶቹ እንደ ምክንያቱ ሊለያዩ ይችላሉ።
በዋነኝነት ግን ተከታዮቹ ምልክቶች ይታያሉ።
• የድካም ስሜት
• አቅም ማጣት
• የትንፋሽ ማጠር
• የመልክ መገርጣት ወይም ነጭ መሆን
• እንደ በሽታው አይነት የአይን እና ቆዳ ቀለም ቢጫ መሆን
• የማዞር ስሜት
• ራስ ምታት
• የትኩረት ማጣት – በተለይ ህጻናት ላይ ትምህርት የመማር አቅማቸውን እና የማስታወስ ችሎታቸውን ይጎዳል።
አንዳንድ ጊዜ ምንም ምልክት ላይኖር ስለሚችል በቤተሙከራ በምርመራ ብቻ ሊታወቅ ይችላል።
እንደ አለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አገላለጽ በቤተ ሙከራ የደም ምርመራ የደም ማነስ አለ የምንለው ለወንዶች የሄሞግሎቢን መጠን ከ13 mg/dl በታች ሲሆን ለሴቶች ደግሞ ከ 12 mg/dl በታች ሲሆን ነው።
ይህ ቁጥር እንደ እድሜያችን፣ የእንቅስቃሴያችን አይነት እና የምንኖርበት ቦታ ሊለያይ ይችላል፤ ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ ወይም ተራራማ ቦታዎች በሚበዙበት ቦታ የሄሞግሎቢን መጠን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

የደም ማነስ ህክምናው
የደም ማነስ በግዜ ካልታከመ ዘላቂ ችግር ሊያመጣ ይችላል። ህክምናውም እንደ ምክንያቱ ይለያያል።
የብረት ንጥረ ነገር እጥረት ያለባቸዉ ከምግብ ጋር ወይም በእንክብል መልክ ንጥረ ነገሩን እንዲያገኙ በማድረግ ህክምና ማግኘት አለባቸው።
የብረት ንጥረ ነገር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች ለምሳሌ
• ቀይ ስጋ
• ዓሳ
• ባቄላ
• ጥቁር ጎመን
• አተር የመሳሰሉት የደም ማነስን ለመከላከል ይጠቅማሉ ።
እንደሁኔታው ሀኪም የብረት ንጥረ ነገር የያዙ እንክብሎችን ሊያዝ ይችላል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top