36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስኬት የታየበት ነው -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

1 Yr Ago 764
36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስኬት የታየበት ነው -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ከ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የተሳካ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም ገለጹ።
አምባሳደር መለስ በዲፕሎማሲው መስክ በሳምንቱ በተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአዲስ አበባ የተካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በጉባኤው 358 የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች የተሳተፋበት መሆኑን ጠቅሰው ከአቀባበል ጀምሮ በቆይታቸውና እስከ ሽኝቱ ያማረ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመደበኛ በረራ በተማሪ 43 የቻርተር በረራዎች መደረጋቸውን አስታውሰው በርካታ እንግዶች የታደሙበት ነበር ብለዋል።
በመሆኑም ከ53 የአፍሪካ አገራት በተጨማሪ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋልን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ተወካዮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
ከህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተገኙበት ውይይት መደረጉን አንስተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ፥ በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የእንግዳ አቀባበል መስተንግዶና ሽኝቱ ጭምር የተቀናጀና የአገርን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወቃል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top