36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለፀ

1 Yr Ago
36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለፀ
በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 42ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር፣ የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ ለማድረግና ፀጥታን የማስከበር ስራውን ምቹ በማድረግ ረገድ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ግብረ ኃይሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መስሪያ ቤትና እንግዶቹ በሚያርፉባቸው ሆቴሎች ጊዜያዊ ቢሮ በመክፈት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ጋር በመቀናጀት መሪዎቹ ወደ ሀገራችን ሲገቡ የአቀባበል ስነ-ስርዓቱንና የስብሰባውን ሂደት በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን ጠቁሟል፡፡
ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፤ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፤ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፤ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተውጣጣው የጋራ ግብረ-ኃይል እንግዶቹ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ አስፈላጊውን ጥበቃና እጀባ ማድረጉን አንስቶ ጥበቃውን ለማሳለጥ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታገዙንም ገልጿል።
ሌሎች የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎችም ጉባኤው በማንኛውም የፀጥታ ችግር እንዳይደናቀፍ አስቀድመው በተሰማሩበት የፀጥታ ሥራ ኃላፊነታቸውን በመወጣት የተጠናከረ ጥበቃና ፍተሻ ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አንስቷል።
እንግዶቹ ወደ ሀገራችን ከገቡ ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት የፀጥታና ደኅንነት ችግር ሳይገጥማቸው የጋራ ግብረ ኃይሉ እንግዳ አክባሪ ከሆነው ከመላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እና ከተቀረው የሀገራችን ህዝብ ጋር በመቀናጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የፀጥታ ተግባር ማከናወን መቻሉንም ገልጿል፡፡
መላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችንን በማሳየት እንግዶቹ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ታላቅ አክብሮት በመስጠትና እንግዶቹ የሚያልፉባቸው መንገዶች ሲዘጉ ለፀጥታ ኃይላችን ከፍተኛ ትብብር በማድረግ የፀጥታ ኃይሉ የሚሰጠውን መመሪያ በመቀበል ትብብራቸውንና አጋርነታቸውን በማሳየት የከተማችን ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ ስለአደረጉ እንዲሁም በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በስኬት ለተወጡ ለመላው የፀጥታና ደህንነት አመራሮችና አባላት የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የላቀ ምስጋና አቅርቧል፡፡
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top