በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን እውን ለማድረግ የደህንነት ትብብርን ማጠናከር ይገባል - ዶክተር አብርሃም በላይ

1 Yr Ago
በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን እውን ለማድረግ የደህንነት ትብብርን ማጠናከር ይገባል - ዶክተር አብርሃም በላይ

በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን እውን ለማድረግ የጸጥታና ደህንነት ትብብርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ። 

31ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የጸጥታና ደህንነት የሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። 

የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፥ በአፍሪካ አህጉር በተለይ በምስራቅ አፍሪካ እያጋጠሙ ያሉ የጸጥታ ችግሮች፣ ቀጣናዊና ውስጣዊ የግጭት አፈታት፣ ሰላም ማስፈንና ቀጣናዊ መረጋጋትን በማጠናከር በኩል የሚስተዋሉ ውስንነቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

የሚስተዋሉ ችግሮች እና ውስንነቶች በቀጣናው የሚፈለገውን እድገትና ብልጽግና ለማምጣት እንቅፋት እንደሆነና የአባል አገራትን የተጠናከረ ጥረት እንደሚጠይቅ  አመልክተዋል። 

በመሆኑም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የጸጥታና ደህንነት ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል። 

አፍሪካውያን የሚያጋጥማቸውን ውስጣዊ ችግር በባህላዊ መንገድ የመፍታት የዳበረ ልምዳቸውን መዋቅራዊ ቅርጽ እንዲይዝ በማድረግ በቀጣናው ለሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮች ጠንካራ የጸጥታና ደህንነት አሰራር ለመዘርጋት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ይህም እውን የሚሆነው የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን ለመፍታት በትኩረት ሲሰራ እንደሆነም ዶክተር አብርሃም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል። 

ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲመክር የቆየው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ  ኃይል አጠቃላይ ስብስባ ዛሬ ይጠናቀቃል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top