የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዘንድሮው በጀት ዓመት በ7.5 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፦ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር

1 Yr Ago
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዘንድሮው በጀት ዓመት በ7.5 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፦ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘንድሮ በ7.5 በመቶ ዕድገት የሚመዘገብበት መሆኑን የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንደሚያመላክት የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።
በመድረኩም የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና የዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ፣ በ2014 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚየ 6.4 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት ደግሞ በ7.5 በመቶ ዕድገት የሚመዘገብበት መሆኑን የስድስት ወራት አፈፃፀሙን መነሻ በማድረግ አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡት ውጤቶች ደግሞ ይመዘገባል ተብሎ ለተቀመጠው ዕድገት እውን መሆን አመላካች ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
የግብርናው ዘርፍ ዕድገቱን በማስቀጠል ረገድ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሴክተር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት የ6.7 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል ብለዋል።
የግብርና ዘርፍ የወጪ ንግድን በመደገፍ ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በውስጣዊ ችግሮች እና ውጫዊ ጫናዎች ከፍተኛ ፈተና ገጥሞት የነበረው የኢንዱስትሪ ዘርፍም ዘንድሮ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የ8.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል።
ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚገኘው የአገር ውስጥ ገቢም ከፍተኛ አፈጻጻም ካስመዘገቡት መካከል ይጠቀሳል ብለዋል።
በስድስት ወራት ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 222 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገቢ መገኘቱን ጠቁመው፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ28.9 በመቶ ዕድገት እንዳለው ተናግረዋል።
የወጪ ንግድ አፈጻጸም መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳይም ከዘርፉ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው አፈጻጸሙ ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር 77 በመቶ መሆኑንም ዶ/ር ፍጹም አብራርተዋል።
በዓለም ገበያ ያለው የምርቶች ዋጋ ተገማች አለመሆን፣ የሕገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ መስፋፋት፣ በንግድ ሰንሰለቱ ያሉ ማነቆዎች እና ሌሎች ተያያዠ ችግሮች የወጪ ንግድ ዘርፍ ፈተናዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህም በተለይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ሚና ያበረክታል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 1.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ጨምረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top