የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት አስደንጋጭ ቢሆንም፤ ነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በዚህ ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

1 Yr Ago
የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት አስደንጋጭ ቢሆንም፤ ነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በዚህ ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ሪፖርት እና ዋና ዋና ግኝቶች ዙሪያ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መግለጫ ሰጥተዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርት እና ምዘና ስርዓት በርካታ ብልሹ አሰራሮች እንደነበሩበት ያነሱት ሚንስትሩ፤ የአሁኑ የፈተና ስርዓት ይህን ብልሹ አሰራር ለማረም የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ብለዋል።
የፈተናው አሰጣጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ እንደሆነ አንስተው፤ በስኬት ለመጠናቀቁ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ፈተናው ሙሉ ለሙሉ ከስሮቆት የፀዳ እንደነበረም ተነስቷል።
በጠቅላላ የተመዘገቡት ተፈታኞች ቁጥር 985,354 ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ 92 ከመቶ የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል።
20,170 ተማሪዎች በፈተናው ከተገኙ በኋላ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች ምክንያት ተባረዋል።
የዚህ ዓመት ውጤት አንድምታ ሲታይ፥ ለዓመታት ከትውልድ ትውልድ ሲንከባለል የተሻገረውን እና ተሸፋፍኖ የቆየውን የትምህርት ስርዓት ብልሽት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው።
ለዚህም መንግሥት የትምህርት ስርዓቱን ባለማሻሻል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ባለመከታተልና በሥነምግባር ባለመቅረፅ፣ ትምህርት ቤቶች እና ባለሀብቶች በጋራ የወድቀቱ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።
ከላይ የተጠቀሱ አካላት ቀጣይ መፍትሄዎች ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዩኒቨርስቲ ከሚቀላቀሉት እና መደበኛ ኮርስ ከሚጀምሩ 29,909 ተማሪዎች ውጭ ያሉ ሌሎች ከ100 ሺህ የሚልቁ ተማሪዎች በውጤታቸው ተለይተው እንደ ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም እየታየ ለአንድ ዓመት የማሻሻያ ትምህርት ወስደው በድጋሚ እንዲፈተኑ ይደረጋል ብለዋል።
ውጤቱ አስደንጋጭ እንደሆነ እንረዳለን ያሉት ሚኒስትሩ፣ ነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በዚህ ውስጥ ልናልፍ ግድ ይለናል፤ ይህ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በሰለሞን ከበደ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top