በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ አራት ሰዎች ህይወት አለፈ

1 Yr Ago
በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ አራት ሰዎች ህይወት አለፈ
በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ሳጂን ጀማል አህመድ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ በአዳማ ወረዳ አዳማ መውጫ የክፍያ ጣቢያ ነው።
የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-42136 ኦሮ ኤፍ ኤስ አር የጭነት መኪና በአዳማ መውጫ የክፍያ ኬላ ላይ ከቆመው ኮድ-3/ የሰሌዳ ቁጥር 14483 ኦሮ አይሱዙ ጋር በመጋጨቱ ነው ብለዋል።
በአደጋው አንድ የክፍያ ጣቢያ ሠራተኛና በኤፍ ኤስ አር መኪናው ውስጥ የነበሩ ሶስት ሰዎችን ጨምሮ የአራት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን ገልጸዋል።
ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች ውስጥ ሁለት ሴቶችና ሁለት ወንዶች መሆናቸውን ዋና ሳጂን ጀማል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪውን ጨምሮ ሶስት ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ጠቅሰው የአደጋው መንስኤ በፍጥነት ማሽከርከር መሆኑን ገልጸዋል።
አደጋው የደረሰው በ8/5/2015 ዓ.ም ከምሽቱ 4:00 ሳዓት መሆኑን ጠቅሰው በአሽከርካሪዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶ በአዳማ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በአደጋው ምክንያት በአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ የአዳማ ዋና መውጫ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ መሆኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ፤ ደንበኞች በሞጆ 52 ኪ.ሜ፤ 56 ኪ.ሜ እና 60 ኪ.ሜ አማራጭ የጉዞ መስመሮች እንዲጠቀሙ ጠይቋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top