በ5 ዙር ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ከ34ሺ በላይ ተመራቂዎችን አሰልጥኖ በብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሰማራቱን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ

1 Yr Ago 680
በ5 ዙር ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ከ34ሺ በላይ ተመራቂዎችን አሰልጥኖ በብሔራዊ የበጎ  ፈቃድ አገልግሎት ማሰማራቱን የሠላም  ሚኒስቴር  አስታወቀ
በአምስት ዙር ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ከ34ሺ በላይ ተመራቂዎችን አሰልጥኖ በብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሰማራቱን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቋል።
ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በአገር ግንባታ ሂደት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ዜጎች ማፍራት መቻሉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በሠላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ድጋፍ ክትትል ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሙለታ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለፁት “ብሔራዊ አንድነት እና ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ዘላቂ ሠላምን መገንባት” በሚል ዓላማ የተቀረፀው ፕሮግራሙ ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን ብቁ አድርጎ የማውጣት ሂደት አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡
ፕሮግራሙን ስኬታማ ለማድረግም በሚዲያ አጠቃቀም፣ በሀገር ግንባታ፣ በስራ ፈጠራ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በሠላም ግንባታ እና በበጎ አድራጎት ላይ ያተኮሩ የ45 ቀን ስልጠናዎችን ከ10 ወር ነፃ የማህበረሰብ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋር በማጠመር ለሰልጣኞቹ በመስጠት አቅማቸውን ፍሬያማ ለማድረግ መሰራቱንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በዚህም እስካሁን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በአምስት ዙር 34,403 ተማሪዎች ስልጠናውን ወስደው በማህበረሰቡ ውስጥ በሚያደርጉት ቆይታ ትርጉም ያለው ስራ መስራት መቻሉን አመልክተዋል።
በብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ላይ የሚሳተፉ ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋለ ከክልላቸው ውጭ ባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ተመድበው ለ10 ወራት ያህል በሚሰጡት አገልግሎትም ከአዲስ ባህልና ወግ ጋር በመዋሃድ ጭምር ለህይወት ስንቅ የሚሆን ልምድ ይዘው እንደሚወጡም ተመልክቷል ፡፡
አንዳንድ ተመራቂዎች ለዚሁ አገልግሎት በተመደቡበት አካባቢ ንግድ የጀመሩ ፣ ቤተሰብ የመሰረቱ እና ስለ ተመደቡበት ማህበረሰብ ባህል እና ታሪክ መጽሐፍ ያሳተሙ መኖራቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ከዚህ በፊት ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ በሁለት ብሔረሰቦች አዋሳኝ አካባቢዎች የጋራ ልማት ስራዎችን በማቀናጀት ስራ የሰሩ መኖራቸው እና የራሳቸውን ቤተሰብ ጭምር ከተመደቡበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር በማስተዋወቅ እና በማቀራረብ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እየፈጠሩ መሆራቸው የፕሮግራሙ ፍሬ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ይሁንእንጂ አንዳንድ ሰልጣኞች የሠላም ሚኒስቴር ካስቀመጠው አቅጣጫ እና ውል ውጭ “በቋሚነት ስራ ያስቀጥራል” የሚል እምነት ከመያዛቸው ጋር ተያይዞ ቅሬታ የማቅረብ ሁኔታ ቢኖርም፣ የፕሮግራሙን ዓላማ በውል ካለመረዳት የመጣ በመሆኑ ዓላማውን የማስገንዘብ ስራ በመስራት እርምት እንዲወሰድ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡
በቀጣይ ፕሮግራሙን ለብዙዎች ተደራሽ ለማድረግ የነፃ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጊዜውን ከ 10 ወር ወደ 6 ወር ዝቅ በማድረግ እና ካለፉት ዙሮች ትምህርት በመውስድ በተሻለ መልኩ ለመተግበር እየሰራ መሆኑን የሠላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በደጀኔ ገብሬ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top