ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት አጋማሽ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ

1 Yr Ago
ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት አጋማሽ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ
ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት አጋማሽ 8.18 ቢሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የኩባንያውን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለመገናኛ ብዙኃን አቅርበዋል።
ኩባንያው በዓለም ካሉ 781 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች 22ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም በአፍሪካ ካሉ 198 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ መቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የኩባንያው የደንበኞች ቁጥር 70 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ይህ አሐዝ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ከነበረው የደንበኞች ቁጥር የ5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 33.8 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ኩባንያው በውጭ ምንዛሬ ገቢ ከሚያገኝባቸው ምንጮች 64.8 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮ-ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት አጋማሽ 8.18 ቢሊዮን ብር አትርፏል። ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት ያተረፈው 9 ቢሊዮን ብር ነበር።
ኩባንያው በተገበረው የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂ 3.5 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ይህም የዕቅዱን 134 በመቶ ማሳካት የተቻለበት መሆኑን አመላክተዋል።
በተያያዘ ቴሌብር 27.2 ሚሊዮን ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን እስካሁን 217 ቢሊዮን ብር ዝውውር ተፈጽሞበታል።
ከ44 ሀገራት ጋር በመተሳሰር 1.6 ሚሊዮን ዶላር በዓለም አቀፍ ሐዋላ መቀበል ተችሏል።
በቤተልሔም ገረመው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top