የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲ ግንኙነት ከየት ወደ የት?

10 Mons Ago
የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲ ግንኙነት ከየት ወደ የት?
የኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ጊዜ ወደ ላቀ ደረጃ ለመድረሱ መገለጫዎቹ ራሳቸው መስካሪዎች ናቸው።
• ሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው ክፍለ ዘመናትን የተሻገረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ እና ቻይና ይፋዊ የመንግሥት ለመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው ግን እ.አ.አ 1970 ነው።
• ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት ኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ማለትም ዘውዳዊ እና ወታደራዊ የፖለቲካ ሥርዓት አልፋ አሁን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት የምትከተል ብትሆንም የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁኔታዎች ተለዋዋጭነት ሳይዋዥቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበበ መጥቷል።
• እ.አ.አ በ1970 መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲጀምር በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃ/ሥላሴ እና የቻይናው መሪ ማኦ ዜዱንግ መካከል ኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚ እና የቴክኒክ ትብብር ስምምነት ተፈራርመው በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1971 ሁለቱም ሀገራት ኤምባሲዎችን ከፍተዋል።
• እ.አ.አ በ2000 በቻይና እና አፍሪካ መካከል የተቋቋመው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ያጠነከረ ስምምነት ሆኗል።
• በኢኮኖሚው ረገድ ከ2006 ጀምሮ ቻይና የኢትዮጵያ አንደኛ የንግድ አጋር መሆን የቻለች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቤጂንግ ከሚገኘው ኤምባሲዋ በተጨማሪ በጓንዙ፣ ቾንግንግ እና ሻንግሃይ፣ሁዋን ጭምር የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚያመቻቹ ተጨማሪ ቆንጽላዎችን በመክፈት የተጠናከረ የንግድ ትስስር ተፈጥሯል።
• የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መድረሱም ይገለጻል፤ ሆኖም ግን የንግድ ሚዛኑ ወደ ቻይና ያደላ በመሆኑ የቻይና መንግሥት ያንን ከግምት በማስገባት ከታሪፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ ገበያ ዕድል በመስጠት የንግድ ጉድለቱን ለማስተካከል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
• በኢንቨስትመንት ዘርፍ ቻይና በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ያላት ተሳትፎ እጅግ ግዙፍ እንደሆነም ይነገርለታል፤ በተለይ በመሰረተ ልማት ዘርፍ በአነስተኛ ወጪ፣ በጥራት እና በአጭር የጊዜ ገደብ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ አድርጋለች።
• በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ረገድም ቻይና ከሌሎች ሀገራት በላቀ ደረጃ በኢትዮጵያ የተሳተፈች ሲሆን ይህም በኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ጉልህ ሚና ተጨውቷል።
• በኢትዮጵያ የቻይና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት 1 ቢሊዮን ዶላር ከተሻገረ ዓመታት አልፏል።
• ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተሻለ ደረጃ ያላት ሲሆን ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና ፈጣን ፕሮጀክት አፈፃጸም ግንባር ቀደም ሆናለች።
• ቻይና ’One Belt and Road Initiative’ ብላ በዘረጋችው መርሃ ግብር በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ፋይናንስ ግብዓት አቅርቦት ረገድ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማዕከሏ አድርጋ የምትንቀሳቀስ ሲሆን በዚህም ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ግምት ያላቸው 400 የቻይና የግንባታ እና የማምረቻ ዘርፍ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
• ከዚህ በተጨማሪ ቻይና ለኢትዮጵያ በአነስተኛ ወለድ እና የረጅም ጊዜ ብድሮችን በማቅረብ በፋይናንስ ዘርፍ ሁነኛ የኢትዮጵያ አጋር መሆን ችላለች።
• ኢትዮጵያ እና ቻይና በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች በትብብር እየሠሩ ይገኛሉ።
• ኢትዮጵያ ተገቢ ባልሆኑ በአንዳንድ የውጪ አገራት ጫናዎች ሥር በወደቀች ጊዜ ሳይቀር፣ ቻይና ከጎኗ በመቆም ጫናዎቹን በማርገቡ ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተች የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ታማኝ ወዳጅ መሆኗን አስመስክራለች።
• የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ባዋቀሩት ካቢኔ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተደርገው የተሰየሙት አዲሱ ተሿሚ ቺን ጋንግ የመጀመሪያውን የውጭ አገራት ጉብኝታቸውን ሲያደርጉ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነችው ቁልፍ አጋር ኢትዮጵያ የጀመሩት እነዚህን ሁኔታዎች ታሳቢ ያደረጉ እንደሆነ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ።
• የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቺን ጋንግ በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በኢትዮ-ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት፣በቀጠናዊ እና በዓለም አቀፋዊ መድረግ ስለሚኖራቸው ትብብር እና ስልታዊ ግንኑነቶች ማጠናከር ላይ መወያየታቸውን እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ይህንኑ ትብብር የሚያፀና ውይይትና የትግበራ ስምምነት ተፈራርመዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top