ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን መረጃ ያላግባብ በመጠቀሙ 390 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጣ

1 Yr Ago 940
ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን መረጃ ያላግባብ በመጠቀሙ 390 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጣ

ስሙን ወደ ሜታ የቀየረው ፌስቡክ የአውሮፓ ኅብረትን የመረጃ ጥበቃ መርኅን በመጣሱ 390 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጣ።

የተጠቃሚዎቹን መረጃ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ ለማስታወቂያነት ለመጠቀም ፈቃድ የጠየቀበት መንገድ ሕገ ወጥ በመሆኑ ቅጣቱ እንደተጣለበት የአየርላንድ መረጃ ጥበቃ ኮሚሽን ገልጿል።

ሜታ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ላይ ማስታወቂያ ለማስተላለፍ መረጃ የሚሰበስብበት እና የሚጠቀምበትን መንገድ ለመለወጥ ሦስት ወራት አሉት።

ሜታ በውሳኔው “እንዳዘነ” ገልጾ አቤቱታ እንደሚያስገባ ገልጿል። የሰዎች ፍላጎት ላይ አነጣጥሮ የሚተላለፍ ማስታወቂያ (personalised advertising) በገጹ እንዳይተላለፍ ከማድረግ ውሳኔው እንደማያግደውም ገልጿል።

ተቆጣጣሪው አካል እንደሚለው ከሆነ፣ ሜታ ተጠቃሚዎቹ የግል መረጃቸውን እንዲጠቀም “በግድ እንዲፈቅዱ” ጫና ማሳደር የለበትም። ተጠቃሚዎች መረጃቸውን ሜታ እንዲጠቀም ካልፈቀዱ ገጹን ትተው መውጣት እንደሚችሉ በመግለጽ ነው ሜታ ጫና እያሳደረ ያለው።

ፌስቡክ እና ኢንስታግራም የአውሮፓ ዋና ቅርጫፋቸው አየርላንድ የሚገኝ በመሆኑ ነው የአየርላንድ ተቆጣጣሪ ቅጣቱ በሜታ ላይ እንዲጣል ያስቻለው።

ይኸው ተቆጣጣሪ የአውሮፓ ኅብረት ሕግ መከበሩንም ያረጋግጣል።

ፌስቡክ እአአ በ2021 ካስገባው 118 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ከማስታወቂያ የተገኘ ገቢ ነው።

ተቆጣጣሪ አካሉ ከዚህ ቀደምም ሌላ ቅጣት ጥሎ የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ በቅርብ ወራት ውስጥ ሁለተኛው ከፍተኛ ቅጣት ነው።

ኅዳር ላይ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ በበይነ መረብ በቀጥታ በማሾለኩ 265 ሚሊዮን ዩሮ ሜታ ተቀጥቷል።

ሜታ በ2023 የሚጣሉበትን ቅጣቶች ለመሸፈን 2 ቢሊዮን ዩሮ እንደመደበ የአየርላንዱ ተቆጣጣሪ አሳውቋል።

የግል መረጃ ደኅንነት ጥበቃ አቀንቃኝ የሆነው ማክስ ሸርምስ በኦስትሪያ እና ቤልጄም ያሉ ሁለት ተጠቃሚዎችን ወክሎ በ2018 ቅሬታ ካቀረበ በኋላ ነው ተቆጣጣሪው ምርመራ የጀመረው።

ጉዳዩ በአውሮፓ ኅብረት የመረጃ ጥበቃ ሕግ ሥር እንዲታይም ተደርጓል።

ፌስቡክ እና ኢንስታግራም የግለሰቦችን መረጃ ለማስታወቂያ የሚጠቀሙበትን መንገድ ሲያሻሽሉ ተጠቃሚዎች “እስማማለሁ” የሚል ቁልፍ ከመጫን ውጪ አማራጭ አይሰጣቸውም።

ቅሬታ ያቀረበው ቡድን ይህ የሜታ አሠራር ተጠቃሚዎች ላይ ጫና ማሳደር ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

መረጃው በምን መንገድ ለማስታወቂያ እንደሚውል ለተጠቃሚዎች ሜታ ግልጽ መረጃ እንዳልሰጠም አክለዋል።

የሜታ ቃል አቀባዮች፣ ውሳኔውን ይግባኝ እንደሚሉ ገልጸው፣ ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ የድርጅቱ ጫና ሥር እንዳልወደቀ እና ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን ፍሰት መቆጣጠር የሚችሉበት ምርጫ እንዳላቸውም ተከራክረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top