ሩሲያ ወታደሮቼ ሞባይል ስልክ በመጠቀማቸው በጠላት ዒላማ ሆኑ አለች

1 Yr Ago
ሩሲያ ወታደሮቼ ሞባይል ስልክ በመጠቀማቸው በጠላት ዒላማ ሆኑ አለች

ሩሲያ ከቀናት በፊት በሚሳኤል ጥቃት 89 ወታደሮቼ የተገደሉብኝ ሞባይል ስልካቸውን እየተጠቀሙ ስለነበረ ነው አለች።

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዩክሬን በሩሲያ በኃይል ተይዞ በሚገኘው ዶኔስክ ግዛት ውስጥ ባለ የምልምል ወታደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሳ ነበር።

የሩሲያ ጦር ጠላት የወታደሮቹን መገኛ መለየት የቻለው ወታደሮቹ የተከለከለውን ሞባይል ስልክ እየተጠቀሙ ስለነበረ ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል።

እስካሁን በዚህ ጥቃት የተገደሉ እና የቆሰሉ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥርን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይቻልም ዩክሬን የሞቱ 400፤ የቆሰሉት ደግሞ 300 ናቸው ብላለች።

ሩሲያ የሟቾችን ቁጥር አሳንሳ የተገደሉበን ወታደሮች ቁጥር 89 ነው ብላለች። በዚህ ጦርነት በአንድ ጥቃት በርካታ ወታደሮች እንደተገደሉባት ሩሲያ ስታምን ይህ የመጀመሪያዋ ነው።

የሩሲያ ጦር እንዳለው እሁድ ታኅሣሥ 23/2015 ዓ.ም. ከእኩለ ለሊት በኋላ በአሜሪካ ሰራሹ ሂማረስ 6 ሮኬቶች ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያው ተተኩሰው ነበር

ማሰልጠኛ ተቋሙ ላይ ከተተኮሱ ሮኬቶች መካከል ሁለቱን መትቼ ብጥልም የማሰልጠኛ ተቋሙ ምክትል ኮማንደር በጥቃቱ ከተገደሉት የጦር አባላት መካከል አንዱ ናቸው ብላለች የሩሲያ ጦር ጨምሮ እንደገለጸው ክስተቱን በተመለከተ ኮሚሽን ተቋቁሞ ጥልቅ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፤ የጦር አባላቱ በጠላት ኃይል ዒላማ የተደረጉት በርካታ ሞባይል ስልኮች ጥቅም ላይ በመዋላቸው ስለመሆኑ ግን ግልጽ ነው ብሏል

የዩክሬን ጦር መሳሪያዎች ጥቃት ማድረስ በሚችሉበት ቀጠና ውስጥ ሆነው የሩሲያ ወታደሮች ሞባይል ስልክ መጠቀማቸው፤ “ጠላት የጦር አባላት መገኛ እንዲለይ እና የሚሳኤል ጥቃት እንዲያደርስ ምክንያት ሆኗል” ብሏል።

ተመሳሳይ ክስተት እንዳይከሰት ጦሩ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፈ ሲሆን በማሰልጠኛ ተቋሙ ላይ ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ የሚሆኑት ለፍርድ ይቀርባሉ ብሏል።

ዩክሬን ጥቃት ስታደርስ ማሰልጠኛ ተቋሟ በምልምል የሩሲያ ወታደሮች የተሞላ ነበር። እነዚህ ምልምል ወታደሮች ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጥሪ አድርገው ጦሩን የተቀላቀሉ 300 ሺህ ወታደሮች አካል ናቸው።

አንዳንድ የሩሲያ ፖለቲከኞች ጦሩ ምልምል ወታደሮችን ለጠላት ኃይል ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ ማቆየት አልነበረበትም ሲሉ እየተቹ ነው።

ሩሲያ በኃይል በያዘችው ዶኔስክ የቀድሞ መሪ የነበሩት ፓቬል ጉብሬዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር አባልን በአንድ ሕንጻ ማቆየት “ወንጀል የሆነ ቸልተኝነት ነው” ሲሉ ነቅፈዋል።

“ማንም ሰው የማይጠየቅ ከሆነ የከፋ ይሆናል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top