አልዛይመር ተብሎ የሚጠራውን ‘የመርሳት በሽታ’ በደም ምርመራ ብቻ ማወቅ የሚያስችል ግኝትን ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ

1 Yr Ago
አልዛይመር ተብሎ የሚጠራውን ‘የመርሳት በሽታ’ በደም ምርመራ ብቻ ማወቅ የሚያስችል ግኝትን ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ
አልዛይመር ተብሎ የሚጠራውን ‘የመርሳት በሽታ’ በደም ምርመራ ብቻ ማወቅ የሚያስችል ግኝት ላይ መድረሳቸውን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ።
አልዛይመር የተለመደ የመርሳት ህመም ዓይነት ቢሆንም ምርመራው በተለይም በህመሙ ጅማሮ አካባቢ በጣም ፈታኝ ሆኖ መቆየቱን የዘጋርዲያን ዘገባ አመልክቷል።
ከዚህ በፊት አንድ ሰው በአልዛይመር መጠቃቱን ለማወቅ በጣም ውድ የሆነው የጭንቅላት ስካን ወይም ከባድ ህመም በታካሚው ላይ የሚፈጥረውን የአከርካሪ አጥንት ኦፕሬሽን አድርጎ የፈሳሽ ናሙና በመውሰድ ይሰራ ነበር። በአዲሱ የተመራማሪዎች ግኝት ግን በቀላሉ በደም ናሙና ብቻ የህመሙ መኖር አለመኖር በምርመራ ማረጋገጥ ያስችላል ነው የተባለው።
በጥናቱ ላይ የተሳተፉት የፐንሲልቬንያ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ቶማስ ካሪካሪ እንደሚሉት አሁን ላይ ያለው የኤም አር አይ (MRI) እና የፒኢቲ (PET) ስካን ምርመራዎች እንደ አሜሪካ ባሉ ሃገራት እንኳ ተደራሽነቱ በጣም አነስተኛ ነው።
አስተማማኝ የደም ምርመራ እድገት በህመሙ ላይ ለሚደረጉ የህክምና ክትትሎች አንድ ደረጃን ከፍ የሚያደርግ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ካሪካሪ፣ የደም ምርመራ ርካሽ፣ደህንነቱ የተጠበቀ እና ለመመርመር ቀላል እንደሆነ ያነሳሉ።
አሁን ላይ ያለው የደም ምርመራ በደም ዉስጥ የሚገኙት ‘አሚሎይድ’ እና ‘ታው ፕሮቲኖች’ የሚያሳዩትን ያልተለመዱ ባህሪያት በትክክል ማመላከት ይችላል የተባለ ሲሆን ለአዕምሮአችን ቅርብ የሆኑ ነርቭ ሴሎችን ጉዳት ማመላከት ግን አሁንም የምርምሩ ፈተና ሆኗል።
ፕሮፌሰር ካሪካሪ እና ከመላው ዓለም የተወጣጡት ተመራማሪዎች አሁንም የአልዛይመር በሽታን በቀጥታ ለማመላከት ከአእምሮ የተገኘ ‘ታው’ የተባለ ልዩ የፕሮቲን ዓይነት ልየታ ላይ ያተኮረ የደም ምርመራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
ተመራማሪዎቹ በተለያዩ የአልዛይመር ህመም ደረጃዎች ላይ በሚገኙ 600 ታካሚዎች ላይ ይህን ሞክረው የፕሮቲን መጠናቸው በአከርካሪያቸው አካባቢ ካለው የ’ታው’ መጠን ጋር እንደሚዛመድ እና አልዛይመርን ከሌሎች የኒውሮዲጄኔሬቲቭ በሽታዎች መለየት እንደሚችል አረጋግጠዋል።
ቀጣዩ እርምጃ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ እና በተለያዩ የማስታወስ ችሎታ ደረጃዎች ወይም ሌሎች የመርሳት በሽታ ምልክቶች የሚሠቃዩትን ጨምሮ በሰፊ ታካሚዎች ውስጥ ሙከራውን ማረጋገጥ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር ካሪ ካሪ በቀጣይ በደም ዉስጥ የሚገኘውን ከአዕምሮ የሚመነጭ የ’ታው’ መጠንን መከታተል ለአልዛይመር ህመም መድሃኒቶችን ለማግኘት እንደሚረዳ ተስፋ ሰጪ ፍንጮች አሉ ማለታቸውን የዘጋርዲያን ዘጋባ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top