የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የተዘረጋበት ብረት ሲዘርፉ የተገኙ ግለሶቦች እጅ ከፈንጅ ተያዙ

1 Yr Ago
የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የተዘረጋበት ብረት ሲዘርፉ የተገኙ ግለሶቦች  እጅ ከፈንጅ ተያዙ
የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የተዘረጋበት ብረት ሲዘርፉ የተገኙ ግለሶቦች የተወሰኑት እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። ከባህርዳር ከተማ ጎርደማ ሰብስቴሽን ተነስቶ ወደ ዳንግላ እና ፓዊ ሰብስቴሽኖች የተዘረጋው የ66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ መሸንቲ ከተማ አካባቢ የታወር ብረቱን ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች መካከል አንዱ እጅ ከፍንጅ መያዙን ተጠቁሟል። የባህርዳር ዲስትሪክት ሰብትራንስሚሽን ኃላፊ አቶ ፈለቀ ዳኛው እንደገለፁት፣ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች ለሌላ ስራ በሚጓዙበት አጋጣሚ ዘራፊዎች ድርጊቱን ሲፈፅሙ አይተው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል። ዘራፊዎቹ ሶስት የነበሩ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ ሁለቱ ሲያመልጡ አንዱን ከአካባቢው የፀጥታ ኃይል ጋር በመተባባር ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ በመያዝ በባህርዳር 8ተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩን ጠቁመዋል። የተሰወሩትን ዘራፊዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ለማዋል የመሸንቲ አካባቢ የፀጥታ ኃይሎች ክትትል እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመለክታል። የከፍተኛ መስመሩ ከፊል ምዕራብ ጎጃምን እና አዊ ዞንን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፤ መስመሩ ተደጋጋሚ ስርቆት ሲፈፀምበት የነበረ በመሆኑ በዚህ መጋቢ መስመር ኤሌክትሪክ የሚያገኙት ደንበኞች ላይ ከፍተኛ መጉላላት እያስከተለ መሆኑንም ተናግረዋል። አቶ ፈለቀ አክለውም የተጎዳውን ማስተላለፊያ መስመር በአሁን ወቅት ጥገና እየተደረገለት እንደሆነም አስታውቀዋል። በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ዝርፊያና ውድመት አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሰ በመሆኑ፤ ሁሉም የሚመለከተው አካል መሰረተ ልማቱን ከእኩይ ዓላማ ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።
 
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የተመረጡ አጫጭር የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የቲክቶክ አካውንታችንን ይከተሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top