በሕፃናት ላይ የሚፈጠር የስኳር ሕመም ምልክቶች፣ መከላከያ ዘዴዎች እና ሕክምና

10 Mons Ago
በሕፃናት ላይ የሚፈጠር የስኳር ሕመም ምልክቶች፣ መከላከያ ዘዴዎች እና ሕክምና
የስኳር ሕመም አዋቂዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ሕፃናትም ላይ ይከሰታል ፡፡ ስኳር በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊከሰት ይችላል። የዓይነት አንድ ስኳር ሕመም በየትኛውም የሕፃናት ዕድሜ ሊከሰት ቢችልም ከ4-6 ዓመት እና ከ10-14 ዓመት ባለው ዕድሜ ክልል የመከሰት ዕድሉ ይጨምራል። ዓይነት አንድ ስኳር በሽታ ትክክለኛ መንሥኤው ምን እንደሆነ አይታወቅም። ነገር ግን የዓይነት አንድ ስኳር በሽታ ያለባቸው በርካታ ሰዎች ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያ እና ቫይረስን የመሳሰሉ የሚከላከለው የሰውነት የመከላከል ሥርዓታቸው በስህተት በጣፊያ ውስጥ የሚገኙትን ኢስሌት የተባሉ ኢንሱሊን አመንጪ ሕዋሳትን እንደሚያወድሙ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የዘረመል እና የከባቢያዊ ተፅዕኖዎች የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይታሰባል። በጣፊያ ውስጥ ያሉ የኢስሌት ሕዋሳት ሲወድሙ ሕፃናት እጅግ አነስተኛ ወይም ምንም የኢንሱሊን ሆርሞን በውስጣቸው አይኖርም። የስኳር ህመም በዘር የመተላለፍ ዕድል ያለው ሲሆን ከዓይነት አንድ ይልቅ ዓይነት ሁለት ስኳር በዘር የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።  የስኳር በሽታ ሥር የሰደደ የጤና ችግር ሲሆን ይህም በሰውነት ውስጥ ምግብን በተለይም ስኳርን (ካርቦሃይድሬትን) ወደ ሰውነታችን ኃይል የመቀየር ችሎታ ላይ ችግር ይፈጥራል።
ከስኳር ህመም ጋር በተያያዘ ሕፃናት ላይ በቀዳሚነት የሚታዩ ምልክቶች:-
● ሽንት ቶሎ ቶሎ መሽናት፣ በተለይም በምሽት ላይ፣
● ተኝቶ ሽንት ማምለጥ፣
● ውኃ ቶሎ ቶሎ መጠጣት፣
● ምግብ ቶሎ ቶሎ መብላት፣
● የድካም ስሜት፣
● ክብደት መቀነስ ወይም ዕድገት ማቆም፣
● በሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ፣
● የማቅለሽለሽ ስሜት ናቸው።
ዓይነት አንድ የስኳር በሽታን ለመመርመር በአንጻራዊነት ቀላል ነው፡፡
ልጆች ላይ ዓይነት አንድ የስኳር በሽታ ምልክቶች ካጋጠሙ የሚደረጉ ምርመራዎች፦
● በማንኛውም ሰዓት በሚደረግ የስኳር መጠን ምርመራ - በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን 200 ሚሊግራም በዴሲሊተር (ሚግ/ዲኤል)፣ ወይም 11.1 ሚሊሞል በሊትር (mmol/L) ወይም ከዚያ በላይ መሆን የስኳር ሕመምን ያሳያል።
● የA1C ምርመራ፦ ይህ ምርመራ ላለፉት 3 ወራት የልጅዎ አማካይ የደም ስኳር መጠንን ያሳያል። በሁለት የተለያዩ ምርመራዎች ላይ የA1C ደረጃ 6.5% ወይም ከዚያ በላይ የስኳር በሽታን ያሳያል።
● ከቁርስ በፊት በሚደረግ የስኳር መጠን ምርመራ - ለ8 ሰዓት ያህል ምግብ ሳይበላ የሚደረግ ምርመራ ነው። የደም የስኳር መጠን ምርመራ ከ126 ሚ.ግራም/ዴ.ሊ. እና ከዚያ በላይ መሆን የስኳር በሽታን ያሳያል።
ለዓይነት አንድ የሚሰጡት የስኳር በሽታ መከላከያ ዘዴዎች እና ሕክምና፦
● ኢንሱሊን መውሰድ፣
● የስኳር መጠንን መከታተል፣
● ጤናማ ምግቦችን መመገብ፣
● አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ናቸው፡፡
 
የመረጃው ምንጭ - ከአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እኔ ሌሎች የጤና ምንጮች የተጠናቀረ)
ግብረመልስ
Top